Saturday, January 5, 2013

መጋቤ ሐዲስ ኃይለ ሚካኤል

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤ አሜን፡፡
ዋኅድ ዜና ሕይወት ወኅልፈት 
 ለክቡር  አባታችን   ኃይለ ሚካኤል
 ዘደብረ ሃይማኖት መካነ ኢየሱስ ዓባይ
ክቡር ሞቱ ለጻድቅ በቅድመ እግዚአብሔር፤ የጻድቅ ሞት በእግዚአብሔር ፊት የከበረ ነው፡፡/ መዝ 115፤6/
ቅድስት ይእቲ ኢየሩሳሌም ሀገረ ዳዊት መቅበርት፤
እስመ በውስቴታ ተሦአ ኃይለ ሚካኤል መሥዋዕት፡፡ ( በዕለቱ የቀረበ ጉባኤ ቃና ቅኔ)

መጋቤ ሐዲስ መምህር ኃይለ ሚካኤል ከኣባታቸው ከአቶ አስፋው ማሩ ( በስመ ክርስትናቸው ሣህለ ማርያም) እና ከእናታቸው ከወ/ሮ ተዋበች ካሣ ( በስመ ክርስትናቸው ወለተ ኢየሱስ)  በድሮው ወሎ ጠቅላይ ግዛት በአሁኑ ደቡብ ወሎ ሀገረ ስብከት አማራ ሳይንት ውስጥ ምስካበ ቅዱሳን ገዳም ሕዳር 12 ቀን 1923 ዓ.ም. ተወለዱ፡፡ በተወለዱ በዐራት ዐመታቸው ጀምረው በገዳሟ ከነበሩት መምህር ፋንታ ከፊደለ ሐዋርያ አንሥተው ዳዊት ደግመው ግብረ ዲቁናውን አጠናቅቀው በሰባት ዐመታቸው ከብጹዕ አቡነ ይስሐቅ ዲቁና ተቀበሉ፡፡ ከዚያ ጊዜ አንስተው ገዳሟን በዲቁና እያገለገሉ የቅስናውን ጓዝ ካጠኑ በኋላ በገዳሙ ከነበሩት መምህር ገብረ ጊዮርጊስ ቅኔ ተቀኙ፡፡ 
ከዚሁ በማስከተልም በዚሁ ገዳም ጾመ ድጓ፣ ምዕራፍ እና የብሉያት ትርጓሜን ተምረዋል፡፡ ከዚያም በ18 ዐመታቸው በዚያው በምስካበ ቅዱሳን ገዳም መንኩሰው አሁንም ቅስና ከአቡነ ይስሐቅ ተቀበሉ፡፡ በገዳሚቱም በረድእነት( እንጨት በመፍለጥ፤ ውኃ በመቅዳት፤ እርሻ በማረስና በመሳሰለው) በኋላም ደግሞ በገበዝነት ለሁለት ዓመታት ያህል አገልግለዋል፡፡ ከዚህ አገልግሎት በኋላ ግን እዚያው ሳይንት ውስጥ ወዳሚገኘው መለክደፈር ኢየሱስ በመሔድ ከመምህር ገብረ ጻድቅ ሦስት ዓመት ቅዳሴውን ከነሙሉ ጓዙ አጥንተው አስመስክረዋል፡፡በ1944 ዓ.ም ደግሞ ደሴ ወጥተው ቁምስናውን ከብጹዕ አቡነ ገብርኤል ተቀብለዋል፡፡
መጋቤ ሐዲስ መምህር ኃይለ ሚካኤል  ከዚህ ቆይታቸው በኋላ  በ1947 ዓ.ም. ደቡብ ጎንደር እስቴ ወረዳ ውስጥ ወደሚገኘውና ወላዴ ሊቃውንት መካነ ጉባዔያት ወደ ሆነው ጥንታዊው ደብረ ሃይማኖት መካነ ኢየሱስ ተሻግረው ከስመ ጥሩ የቅኔና የመጻሕፍት ሊቅ መምህር ገብረ ጊዮርጊስ ጉባኤ ገቡ፡፡ ይህን ታላቅ ጉባኤ ከተቀላቀሉ በኋላ ቅኔውን አስፋፍተው መጻሕፍቱን ማሔድ ጀመሩ፡፡ በአምስት ዐመት ቆይታቸውም ሐዲሳትን በሙሉ ፤ውዳሴ ማርያምና ቅዳሴ ማርያም ትርጓሜ፣ ፍትሐ ነገሥት፣ባሕረ ሐሳብ፣ ኪዳንና ትምህርተ ኅቡአት ትርጓሜን አጠናቅቀው ተምረዋል፡፡
በወቅቱ ንግሥተ ንግሥታት ዘውዲቱ በአንድ ግሪካዊ መሐንዲስ ያሠሩት የደብረ ሃይማኖት መካነ ኢየሱስ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን  በጣልያን ከተቃጠለ በኋላ ዳግመኛ በንጉሠ ነገሥቱ ቀዳማዊ ዐጼ ኃይለ ሥላሴ ትዕዛዝ በታላቁ አቡነ ሚካኤል አስተባባሪነት ተሠርቶ ተጠናቅቆ ስለነበርና እቦታው ላይ ተቀምጠው ያሠሩት የነበሩት በዚሁ ቦታ ተምረው ከጣልያን ወረራ በኋላ ግብጽ ወርደው ከተሾሙት አምስቱ ሊቃነ ጳጳሳት አንዱ የነበሩት ብጹዕ አቡነ ሚካኤል ሊቀ ጳጳስ ዘጎንደር ሁል ጊዜ እንደሚያደርጉት መስከረም 21 ቀን ወደተወለዱባትና ወደ አደጉባት ግሸን ማርያም ሊሳለሙ ሔደው በዚያው አርፈው ስለተቀበሩ ለምርቃቱ የመጡት የኋላው ፓትርያርክ  አቡነ ቴዎፍሎስና የትግራዩ ታላቁ አቡነ ዮሐንስ ነበሩ፡፡ በዚህ ጊዜ የጉባኤውን ታላቅነትና የመምህሩን ሊቅነት የተመለከቱት አቡነ ዮሐንስ መምህር ገብረ ጊዮርጊስን አግባብተው ወደ ትውልድ አካባቢያቸው አክሱም እንዲሔዱ ሲያደርጉ መምህር ኃይለ ሚካኤል በዚያው ዓመት በ1952 ዓ.ም. ጉባኤውን ተረክበው ማስተማር ጀመሩ፡፡
እንደ የኔታ ትውስታ ጉባዔውን ከመረከባቸው አንድ ዓመት ቀደም ብሎ ንጉሠ ነገሥቱ እቦታው ድረስ በሄሊኮፕተር መጥተው ቤተ ክርስቲያኑንና አብያተ ጉባኤያቱን ጎብኝተዋል፡፡ በጊዜው ቅኔና የመጻሕፍት የሚማር ብቻ 400 የሚደርስ ተማሪ ስለነበር ተማሪዎቹ ለንጉሡ ደበሏቸውን እያነጠፉ ተቀብለዋቸው ነበር፡፡ ንጉሡ ግን እያስነሱ እያሸከሙ ሳይረገጡት ከመግባታቸውም በላይ ሲመለሱ ለሁሉም የሚዳረስ አንሶላና አቡጀዲ ልከውላቸው ነበር፡፡
መጋቤ ሐዲስ የንታ ኃይለ ሚካኤል ጉባኤውን ከተረከቡ በኋላ ላለፉት ሃምሳ ዓመታት በደብረ ሃይማኖት መካነ ኢየሱስ ወንበራቸውን ሳያጥፉ በማስተማር እጂግ ብዙ ሊቃውንትን ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን አበርክተዋል፡፡ ከ90 በላይ በስም የሚታወቁ ሊቃውንትንም አፍርተዋል፡፡ የቀለም ቀንድ ይባሉ ከነበሩት ከቀድሞው ሊቀ ጉባኤ አስበ (በኋላ አቡነ ኤልያስ ይባሉ ከነበሩትና ከአቡነ ዮሴፍ ጋር በመኪና አደጋ ያረፉት) ጀምሮ አሁንም በሊቃውንት ጉባኤ የሚያገለግሉ በአዲስአበባና ከትግራይ እስከ ሸዋ ድረስ ባሉት ብዙ ጥንታውያን ቦታዎች የሚያገለግሉ ታላላቅ ሊቃውንትን አፍርተው አልፈዋል፡፡
 መጋቤ ሐዲስ የኔታ ኃይለሚካኤል ከዚህም በላይ በደቀ መዛሙርቶቻቸው በትሕትናቸው በሕዝቡም ዘንድ ጭምር ደግሞ በምናነኔያቸው፣ በአስታራቂነታቸው፣ በእንግዳ ተቀባይነታቸውና አንዳንድ ጊዜም በሚደርጉላቸው የማዳን ሥጦታወቻቸው በጉልህ ይታወቃሉ፡፡ በየኔታ ጉባኤ ቤት የከሰዓት በኋላ ጉባኤ ካለ በዚያ አድካሚ በሆነው የመጽሐፍ ጉባኤ ቤት ያለምንም ምግብ ይካሔድ ነበር፡፡ ልክ በገዳም ሥርዓት ራሳቸውን መቁነን አስገብተው ከጉባኤና ከማስታረቅ የተረፈውን ጊዜያቸውን ቅዱሳት መጻሕፍትን በመመልከትና በጸሎት ተወስነው ከበዓታቸው ሳይወጡ በጽናትና በተጋድሎ የኖሩ ታላቅ አባት ነበሩ፡፡ የኔታ ኃይለ ሚካኤል ፍጹም ትሑት ከመሆናቸው የተነሣ ደቀ መዛሙርቶቻቸው በሙሉ በሚባልበት ደረጃ አሁንም ድረስ ምስክርነት የሚሰጥላቸው ትሑታን ናቸው፡፡  በዚህም በዛፉ ብቻ ሳይሆን በፍሬዎቻቸውም የተመሰከረላቸው ናቸው፡፡ ከመናኝነታቸው የተነሣም ብዙ ተአምራት ይደረግላቸው ነበር፡፡በጉባኤ ቤቱ ሥርዓትና በራሳቸው በግላቸውም  በሚካሔደው ያልተቋረጠ ጸሎት የተነሣ ከዚያ በሚገኝ መዝገበ ጸበል እየተጠመቁና እየጠጡ ከሱስ ነጻ ከመውጣት አንሥቶ አንደበታቸው ተዘግቶና ጆሯቸው መስማት ተሥኖት ከኖሩ በኋላ ፈወስ ያገኙ ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ ከተደረገላቸው ገቢረ ተአምራት የተነሣ አሁንም ድረስ ከየሚኖሩበት አካባቢ ቢያንስ በዓመት አንድ ጊዜ ወደ መካነኢየሱስ እየሔዱ በዓል የሚያከብሩት እጂግ ብዙዎች ናቸው፡፡
መጋቤ ሐዲስ የኔታ ኃይለ ሚካኤል ከዚህ በላይ በሕዝቡ ዘንድ የሚታወቁት ለሌላ ሽማግሌ ያስቸገሩትን የትኛውንም ዓይነት ጠበኞች በማስታረቅ ነው፡፡ የኔታ ዘንድ መጥቶ ሳይታረቅ የሚሔድ እስካሁን ድረስ በታሪክ ታይቶ አይታወቅም፤ ዕርቁም ሁል ጊዜ ጸንቶ ይኖራል፡፡ የሚያገረሽ እንኳ ሲያጋጥም እንደገና ጊዜ ወስደው መክረውና ዘክረው የደረቀውንም አለዘበው በፍጹም ዕርቁን ያጸኑታል፡፡ በተለይ በአንድ ወቅት ታቦት ሠርቆ የተገኘን አንድ ካህን እርሱን ብቻውን አስተምረው መክረውና ዘክረው ቀኖናም ሰጥተው ካረሙ በኋላ ከነቤተሰቡ ከሀገራችን ለቅቆ መውጣት አለበት የሚለውን የአንድ ደብር ሕዝብ ያስታረቁበት መንገድ ድርጊቱን ለተመለከቱ ሁሉ ሲያስደንቅ የሚኖር ነው፡፡ ሕዝቡም ከቅዳሴ ውጭ መስቀላቸውን ሳይሳለም ከሔደ የተባረከ አይመስለውም ነበር፡፡፡ ከዚህ የተነሣ በደርግ ጊዜ ተገድዶ በበዓል ሲያርስ የዋለ አንድ ገበሬ ማታ ላይ በሬዎቹን እንደፈታ ቀጥታ ያመራው ወደ የኔታ ኃይለ ሚካኤል ነበር፡፡ ገበሬው የኔታ ሰይፈቱኝ ፀሐይ እንዳትጠልቅ በማለት በሩጫ እንደደረሰ በጊዜው በጉባኤ ቤቱ የነበሩ ደቀ መዛሙርት ይመሰክራሉ፡፡ በሩቅ አድባራት ያሉ ካህናት እርስ በእርስ በቀኖና ሲከራከሩ ወይም ከነፍስ ልጆቻቸው ጋር በተያያዘ አወዛጋቢ ጉዳይ ሲያጋጥም ሕዝቡ ወይም የካህናት ጉባኤው ሽማግሌ ወይም አድራሽ መርጦ ወደ የኔታ ይልካቸዋል፤ እነርሱ ሲደርሱም አቤቱታቸውን ካቀረቡ በኋላ መጽሐፍ ተገልጦ ጥቅሶቹ ወይም የቀኖና መጻፍቱ አንቀጾቹ እየተነበቡ በእርሳቸው እየተብራሩ መልስ ከተሰጣቸው በኋላ ለላካቸው ሕዝብ ወይም ሰበካ ደብዳቤ ተጽፎ በጉባኤ ቤቱ ማኅተም ከታተመ በኋላ ይላካል፡፡ በዚህ መንገድ የአካባቢውን ሕዝብና አብያተ ክርስቲያናት ችግሮች በሙሉ በመፍታትና በሰላማዊና በመንፈሳዊ ሥርዓት ብቻ በመፈጸም ለሃምሳ ዓመታት ያህል ሳይሰለቹ አገልግለዋል፡፡
ሌላውና የሚደነቁበት ደግሞ መስተንግዶው ነበረ፡፡ በነየኔታ ጉባኤ ቤት ከባለተስፋ የምትሰጠው ገንዘብ ሁሉ በሥርዓት አገልግሎት ላይ ትውል ነበር፡፡ በዓመት ውስጥ በሰፊው ተደግሶ ሲያገለግሉ የዋሉና ያደሩ ሊቃውንት እንግዶችና ሌሎች ምእመናን የሚስተናገዱባቸው ሰባት በዓላት አሉ፡፡ እነዚህም የዘመን መለወጫ፣ የሕዳር ቁስቋም፣ የልደት ( ታቦቱም ኢየሱስ ስለሆነ በዓሉም ቦታው ላይ ብዙ ሕዝብ ከሩቅ ሁሉ መጥቶ የሚያከብረው ስለሆነ)፣ የጥር መርቆሬዎስ ( ሰማዕቱ መርቆሬዎስ ታቦቱ በድርብ ያለ ከመሆኑም በላይ በቦታው በታላቅ ድምቀት ከፈረስ ግልቢያና ከመሳሰሉት የሕዝብ ባሕሎች ጋር የሚከበረው በጥር ሃያ አምስት ነው)፣ የትንሣኤ፣ በዓለ ጴጥሮስ ወጳውሎስ (በተለምዶ የሐምሌ አቦ የሚባለው)፣ እና የፍልሰታ ኪዳነ ምሕረት ናቸው፡፡ ከዚህም በላይ በየወሩ በ29 መጥተው ለሚያስቀድሱ ሁሉ ዝክሩ በየኔታ ጉባኤ ቤት ይዘከራል፡፡ ከዚህ በላይ በዘወትሩ ጊዜ የኔታ ሕጻን ልጅ እንኳ ቢሔድ ሳይስተናገድ አይመለስም፡፡ በመገረም ስንጠይቃቸውም መልሳቸው አንድ ብቻ ነበር፤ ጌታ ሕጻን ልጅ መስሎ ወይም መንገደኛ ወይም ደግሞ የተገበና የማይታዘንለት መስሎ ቢመጣና ቢመለስብንስ የሚል ነበር፡፡ በረድነት ከ40 ዐመት በላይ ያገለገሏቸው የንታ አባ ኪዳነ ማርያም የሚቀርብ ነገር የለም ካሉ እንኳን የኔታ ሀብታም ነው ደሃ ሳይሉ የሻይ መጠጫ ብለው ሳይሰጡና አንድ አቡነ ዘበሰማያት ሳይሰጡ እንዲሁ አሰናብተው አያውቁም፡፡ በአንድ ወቅት ከፍተኛ የሆነ የሳምባ ምች ታምመው ሆስፒታል ያለ ፈቃዳቸው ገብተው በአግባቡ መናገር በማይችሉበት ሰዓት እንኳ አንድ መነኩሴ ከጎናቸው አስቀምጠው ለመጣው ሁሉ ለእያንዳንዱ አቡነ ዘበሰማያት እንዲሰጥ በማድረግ በዚያች ወቅት እንኳ እንዳይቋረጥ ያደረጉ ፍጹም ተወዳጅ አባት ናቸው፡፡
መጋቤ ሐዲስ የኔታ ኃይለ ሚካኤል በአካባቢው የነበሩትን ድብቅ ባዕድ አምልኮዎች ነቅለው ያጠፉ፣ ብዙ የሌላ እምነት ተከታዮችን አስተምረው ያጠመቁና በተለይ ታላላቅ ሸሖች ሳይቀር መጥተው ግራ ያጋባቸውን ሲጠይቋቸው ከዚያው ከቁራኑ ጀምረው ያስረዱ የነበሩ ብዙዎችንም በስውር ወደ ክርስትናና ወደ ምናኔ ከመሩ ጥቂት አባቶች አንዱ ነበሩ፡፡
በዚህም ሳይገደቡ የደብረ ሃይማኖት መካነ ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን በታደሰባቸው ሁለት ጊዜያትም የዐቢይ ኮሞቴው ሰብሳቢ በመሆን ታላላቅ ሥራዎችን አሠርተዋል፤ ቤተ መዛግብቱንም በዘመናዊ መንገድ በአዲስ መልከ አሳንጸዋል፡፡ በቅርብ ርቀት ላይ የምትገኘውንና በጣልያን ጦርነት ወቅት የጣልያን ሠራዊት ምሽግ የነበረችውን የመንበረ ፀሐይ  ጥንጫ ቅድሰት ማርያም ቤተ ክርስቲያንን ሙሉ በሙሉ በማሠራትና ዕቃ ቤትም ጭምር በማሳነጽ፣ የራሷ ገቢ እንዲኖራት በማድረግ ለቦታዋ የሚያገለግሉ መነኮሳትና ዲያቆናትን ከራሳቸው እየከፈሉ ሲያስገለግሉ ቆይተውም ትንሽ ቀረብ ከሚሉት ምእመናን ልጆችም አስተምረው ካህናትንና ዲያቆናትን በማፍራት ቤተ ክርሲያኗን እንድትገለገል በማድረግ ከፍተኛ ኃላፊነት የተወጡ ምስጉን አባት ነበሩ፡፡ በደርግ ዘመን የተወረሱትን የአምቦ ጠበልም ተከራክረው በማስመሰል ሰው ቀርቶ እንስሳትም ፈውስና ደኅነት እንዲያገኙበት አስችለዋል፡፡
የኔታ መጋቤ ሐዲስ ኃይለሚካኤል የታች ቤት ትርጓሜ መሥራች የሆኑት የእነ መምህር ኤስድሮስና የሌሎቹም ታላላቅ ስመ ጥር ሊቃውንት ያስተማሩበትን፤ በመካከለኛው ክፍለ ዘመን በተለይም በዘመነ መሳፍንት ቅባትና ጸጋ ደቀ መዛሙርት ብዙ ቦታዎችን ለማዳረስ ጥረት ባደረጉበት ወቅት ከጎጃሙ ዲማ ጊዮርጊስ ጋራ የመናፍቃን ትንፋሻቸው እንኳ ያልደረሰበት ካልዕ እስክንድርያ እየተባለ የሚጠራውን የመካነ ኢየሱስን ጉባኤ ቤት አሁን በስዊድን ሀገር ከሚገኙት የቦታው ተማሪዎችአንዱ ከሆኑት ከብጹዕ አቡነ ኤልያስና በግሪክ ሀገር ከምትገኘው የመንፈስ ልጃቸው ወይዘሮ መልካሜ በመረዳት ጉባኤ ቤቱንና አዲስ የእንግዳ አዳራሽ አሠርተዋል፡፡ በኋላም በማኅበረ ቅዱሳን ውስጥ ያሉ ልጆቻቸውን በማስተባበር  የጉባኤ ቤቱን ወለል በሲሚንቶ በማሠራትና ለጉባኤ ቤቱ አስፈላጊ የሆኑ ወንበሮች፤ ጠረጴዛ፣ የመጻሕፍት መደርደሪያ ሼልፎች፤ ቁም ሳጥኖችና ሌሎች አስፈላጊ ነገሮችንም  ያደራጁና ለደቀ ማዛሙርትም መጠለያ ቤት ያሠሩ ከዚህም በላይ መምህር ገብረ ጊዮርጊስ ወደ አክሱም ሲሔዱ ባዶውን ትተውት የሔዱትን ጉባኤ ቤት እንደገና በመጻሕፍት እንዲሞላ አድርገውና ለተተኪው አዘጋጅተው የሄዱ ታላቅ አባት ናቸው፡፡
መጋቤ ሐዲስ የንታ ኃይለ ሚካኤል ይህን በመሰለው ተጋድሎ ከኖሩ በኋላ በቅርብ ጊዜ ደግሞ ቅዱሳን በገዳማት ከሚሰጧቸው ተጋድሎዎች አንዱ የሆነውን ደዌ ተቀብለው እርሱንም እንደ ጥሩ ዘመድ በትዕግስት አስተናግደው ታኅሣሥ 16 ከቀን ከቀኑ በ10፡00 ሰዓት ዐርፈዋል፡፡ ደቀ መዛሙርቶቻቸውና በቅርብ ርቀት ያሉት ሊቃውንት እንኳ መሰባሰብ እስኪችሉ ድረስ ተብሎ ለአካባቢው ሕዝብ ሳይነገር በሩቅ ላሉት ብቻ በስልክ ሲነገር ካመሸ በኋላ ሌሊቱን ከበሮ ያልተመታበት (ከሕዘቡ ለመደበቅ ሲባል) ማኅሌትና ሰዓታት  በዚያው በጉባኤ ቤቱና በእንግዳ ቤቱ ተቁሞ አደረ፡፡ በ17 ግን ብዙ ሊቃውንት ስለተሰበሰቡና ለሕዝቡም ስለተነገረ ሥጋቸው ወደ ቤተ ክርስቲያን ገብቶ ለቁጥር የሚያዳገቱ የድጓና የአቋቋም መምህራን ከነደቀ መዛሙርቶቻቸው፣ የቅኔና የመጻሕፍት ትርጓሜ መምህራን ሌሎች ሊቃውንትም ባሉበት ደስ የሚያሰኝ የአርያም ፍትሐት ተቁሞ ለእርሳቸው በሚገባ መጠን በወረብና ነፍሳቸው ሙሽራ መሆኗን በሚያሳይ ሁኔታ ሲሸበሸብ፤ ቅኔም እንደ ወንዝ ተርፎ ሲፈስስ አድሯል፡፡ የቦታው አለቃና የድጓ  መምህር የሆኑት  ምስጉኑ  መልአከ ሃይማኖት የኔታ ሲሳይ አሰፋ በአርያምና አቡን (የድጓ ቀለም ነው) አመራረጥና ቅንብራቸው በሊቃውንቱ ዘንድ ተመስግነውበታል፡፡ ከዚያም ታኅሣሥ 18 ቀን ሙሉ ፍትሐቱና የቅርብ ከተሞችና የአካባቢው ሕዝብ ለቅሶ ከቅጽረ ቤተ ክርስቲያኑ ውጭ ባለው ሰፊ ሜዳ በታላቅ ሥነ ሥርዓት ሲከናወን ከቆየ በኋላ ሊቃውንቱ ‹‹ ነዋ ኃይለ ሚካኤል አቡነ፤ ይስአል ለክሙ ምሕረተ፤ ለእናንተ ምሕረትን ይለምን ዘንድ እነሆ አባታች ኃይለ ሚካኤል›› የሚለውን የመሰናበቻ ወርብ ወርበው አጭር የሕይወት ታሪካቸው ተነብቦ በተመረጡ ሊቃውንት ብቻ ቅኔ ተሰጠ፡፡ ከላይ በመግቢያው ላይ ያለውና ‹‹ ሀገረ ዳዊት ኢየሩሳሌም የተባልሽ የደብረ ሃይማኖት መካነ ኢየሱስ የየኔታ መቃብር ቅድስት ነሽ፤ ኃይለ ሚካኤል የተባለ መሥዋዕት ዛሬ በአንቺ ተሠዉቷልና›› የሚል መልእክት ያለው ጉባኤ ቃና ከቀረቡት ቅኔዎች አንዱ ነበር፡፡ ከዚህ በማስከተልም በጎንደር ከተማ የአራቱ ጉባኤያተ መጻሕፍት መምህርና የመንበረ መንግሥት መድኃኔ ዓለም አስተዳዳሪ በሆኑት ክቡር ሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ ሐዲስ ‹‹ አድኅነኒ እግዚኦ እስመ ኀልቀ ሔር፤ ደግ ሰው አልቋልና አቤቱ አድነኝ›› /መዝ 11፤ 1/ በሚል ረእስ መነሻነት በዕንባ የታጀበ ሰፊ ትምህርት ተሰጥቷል፡፡  ሊቀ ሊቃውንት አሥሩን አንቀጸ  ብጹዓን እየዘረዘሩ ሁሉም በየኔታ ኃይለ ሚካኤል መፈጸማቸውን በሚያውቃቸው፤ በሚወዳቸውና በሚያከብራቸው ሕዝብ ፊት ካስረገጡ  በኋላ  በወንጌል ብጹዕ ተብለዋልና ብፁዕ አባታችን ማለት ይገባናል ብለዋል፡፡ ሊቀ ሊቃውንት  ዕዝራ  ሐዲስ ለልቅሶ ሳይሆን ለበረከት መምጣታቸውን ነግረው ያስለቀሰኝ ዕረፍታቸው ሳይሆን ከዚህ በኋላ በዛራ ሚካኤል  ቅኔና ሐዲሳት ከሚያስተምሩት አረጋዊና ፍጹም መናኝ አባት ከየኔታ ጥበቡ ታየ በቀር ታላላቆቹን አባቶቻችን ማጣችን ነው፤ ስለዚህም ደግ ሰው አልቋልና ለቅሶ ለእኛ ይገባናል እያሉ በማልቀሳቸው ሕዝቡን የበለጠ አስለቅሰውታል፡፡ በመጨረሻም ሥጋቸው ወደ ቤተ ክርስቲያን ተወስዶ ቅዳሴ ተቀድሶና ለታላላቅ አባቶች በሚደረገው ትውፊት መሠረት ታቦት ወጥቶ ከታቦቱ በኋላ ሥጋቸው አብሮ እየዞረ ዑደት ከተደረገ በኋላ የመጨረሻ የማጽናኛ መልእክቶች በሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅና በተመረጡ ሊቃውንት ተሰጥቶ ከቀኑ በዘጠኝ ሰዓት ሥርዓተ ቀብራቸው ተፈጽሟል፡፡ የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ አፈ መምህር ገብረ ሥላሴ ቆቡንና ልብሰ ምንኩስናውን ከእኛም ሆነ ከብዙዎች ማግኘት ያቻላል፤ ምናኔና ቅድስናውን ግን እነ የኔታ ይዘውት ሄደዋል ሲሉ በዐውደ ምሕረቱ ከቆመውና የተለየ ፍቅር ካለው ከዚያ ሕዝብ ዕንባ የማያወርድ አልነበረም፡፡
በተወለዱ በ82 ዓመታቸው ያረፉትና ከልጅነታቸው ጀምሮ ከገዳምና ከቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ሳይለዩ ዕድሜያቸውን ያጠናቀቁት መጋቤ ሐዲስ የንታ ኃይለ ሚካኤል በደብረ ሃይማኖት መካነ ኢየሱስ በኖሩባቸው 58 ዓመታት ውስጥ እኳንስ የትውልድ ስፍራቸውን ሊጎበኙ ቀርቶ ተናግረውትም አያውቁም፤ ቅድስተ ሀገር ኢየሩሳሌም ደርሰውና በዚያው ጠፍተው መንነው ሊቀሩ ሲሉ በሚያውቋቸው ሰዎች ተይዘው ከመጡበት ከዚህ መንገድ በቀርም የትም ሳይጓዙ ኖረዋል፡፡ ነገር ግን ደግሞ  ጉባዔያቸውን አስረክበው ወደ ዋልድባ ገብተው ለመመነን ያላቸው ሀሳብ አንድም ቀን ሳይመክን በጉባኤ ቤቶች መዳከምና በደቀመዛሙርት በየጉባዔ ቤቶች መቀነስ ሲያዝኑና ሲተክዙ የኖሩ አባት ናቸው፡፡ ሆኖም በፈቃደ እግዚአብሔር ሐዲሳቱን ከርሳቸው ብሉያቱን ጎንደር ከመምህር ፀሐይ የተማሩትን የቀለም ልጃቸውን የንታ ሐረገወይን ከሁለት ዓመት በፊት በወንበራቸው ላይ ተክተው በማለፋቸው ሕዝቡም ሆነ ሊቃውንቱ ተጸናንተዋል፡፡ በዕለቱ የነበረው ሕዝብም በሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ አሳሳቢነት የተለመዱትን   በዓመት ውስጥ የሚካሔዱትን ወርኃዊውን በዓለ እግዚእን ጨምሮ የስምነቱን ታላላቅ በዓላት ዝክሮች ለማስቀጠል፣ ጸሎተ ፍትሐታቸውን አሟልቶ ለማዘከርና ተተኪውን መምህር የንታ ሐረገ ወይንን ለመርዳትና ጉባዔ ቤቱን የበለጠ ለማጠናከር ኮሚቴ ሰይሞ ሥራ ጀምሯል፡፡ የመንፈስና የቀለም ልጆቻቸው እንዲሁም ለአብያተ ጉባዔያት የሚያስቡ ሁሉ የድርሻቸውን እንደሚወጡ ይጠበቃል፡፡  
ከበዓታቸው ወጥተው በአስገዳጅ ሁኔታ ወደ ቤተ ክህነት ሲሔዱ እንኳን ከተማውን የማያቋርጡት ይልቁንም ጫካ ጫካውን ዞረው ይሄዱ ከነበሩት ከመኛኑና ከሊቁ ከአስታራቂው ከለጋሱና ከፈዋሹ አባታችን የንታ ኃይለ ሚካኤል፤ ሊቀ ሊቃውን ዕዝራ ሐዲስ በትምህርቱ እያነቡና ሕዝቡንም እያስለቀሱ እንደገለጹት  በእውነት ብጹዕ መባል ከሚገባቸው ከብፁእ  አባታችን  በረከት ያሳትፈን አሜን፡፡

30 comments:

 1. ከብፁእ አባታችን በረከት ያሳትፈን አሜን፡፡

  ReplyDelete
 2. አሜን ከብፁእ አባታችን በረከት ያሳትፈን፡፡

  ReplyDelete
 3. አሜን! በረክታችው በሁላችን ይደርብን! ነፍሳቸውን በአብርሃም አቅፍ ያኑርልን!

  ReplyDelete
 4. ሥጋየን ተመችቶት የእግዚአብሔርን ቃል እንደፈለኩት እንዳልተረጉመው፥ የተጀመረውም ምዕራፍ ሳይቋጭ፥ ተማሪዎቹም የጠየቁት ጥያቂ ሳይመለስ እንዴት ጉባኤው ይጠናቀቃል በማለት በፍስኩ እንኳ ሳይቀር እስክ ፱ እና ፲ ሰዓት ነበር ራሳቸውን ከምግብ የሚከለክሉት።

  ReplyDelete
 5. betqaam yasazenal bande weket lesera Este mekanselam heje bereketachewn agegechalehu serachewnem ayechalehu talake abate neberu!!!!!!!!!!!!!!!!!"abetu dege sew alkwalena"

  ReplyDelete
 6. u×U Ád´“M u¨<’~ ŸJ’ eK ›v %ÃKT>"›?M Ø\ ›É`ÑI ›p`u¤ªM: u›”É ¨pƒ u1993¯.U KY^ ¨Å ˆe‚ H@Î ¾}²[²[¨<” ’Ñ` uS<K< u›Ã’@ }SM¡ŠÁKG<: ˆ’@U ß”k‚” ›"õÁ†¨< ÁÑ–G<ƒ” u[Ÿƒ ²`´_ SÚ[e ›M‹MU:: ›Ó²=ÁwN?` ’õd†¨<” ŸpÆd” Ò` ÁÉ`ÓM”::›u?~ ÅÓ e¨< ›MsM“...
  u}‰K” ›pU ›slS¨<ƒ ¾H@ƃ” Y^ uS<K< ŸˆÓ²=›wN?` Ò` ¾S¨×ƒ S”ðd© %Lò’ƒ ›Kw”

  ReplyDelete
 7. አሜን! በረክታችው በሁላችን ይደርብን! ነፍሳቸውን በአብርሃም አቅፍ ያኑርልን!

  ReplyDelete
 8. ዲያቆን መልአኩ
  ቸሩ መድኃኒዓለም የብፁእ አባታችንን ነፍስ ይማር !!!
  ነፍሳቸውን በአብርሃም በይስሐቅ እና በያዕቆብ አጠገብ ያኑርልን !!!
  አሜን።
  ከብፁእ አባታችን በረከት ያሳትፈን አሜን፡፡

  ReplyDelete
 9. ከብፁእ አባታችን በረከት ያሳትፈን::

  ReplyDelete
 10. አሜን! በረክታችው በሁላችን ይደርብን! ነፍሳቸውን በአብርሃም አቅፍ ያኑርልን!

  01/07/2013 9:57AM

  ReplyDelete
 11. ቆቡንና ልብሰ ምንኩስናውን ከእኛም ሆነ ከብዙዎች ማግኘት ያቻላል፤ ምናኔና ቅድስናውን ግን እነ የኔታ ይዘውት ሄደዋል

  ReplyDelete
 12. እኒህንማ ሞቱ ማለት አይገባም :: የማያልፍ ሥራ ሠርተው ነው ያለፉ:: እንደ እርሳቸው ያሉም ከእርሳቸውም የተሻሉም በእርሳቸው መምህርነት ተወልደው ይሆናል:: 'ካህን በቡትቶ የተጠቀለለ ወርቅ ነው' የሚባለው ለዚህ ነው ለካ! አቀራረብህ መልካም ነው:: ይበል ብያለሁ!! እስኪ እንደእርሳቸው ያሉ የቤተክርስቲያናችንን ሊቃውንት በሕይወታቸው አስተዋውቀን!!

  ReplyDelete
 13. diakon melaku betam azgnalehu.lekelikawnt endalut "deg sew aleke" yemiasegn new.bezeh kifu zemen yenetan matat kealet yekebede hazen new.bete kerestian yalechew bemerewochua sayhon benezeh tselot new.tselotachew be atsede nefsem selehone tesfa anekortem.k.dejene kedenver colorado/usa/

  ReplyDelete
 14. Amen egziabher amlak nefsachewen yemarelen egnanem beberketachewena redetawe yegobegnene

  ReplyDelete
 15. ewunetim "Deg sew alkualina" Egzi abeher deg sew yabizalin.

  ReplyDelete
 16. አሜን በረከታቸው ይደርብን! የአባታችንን የመጋቤ ሐዲስ የንታ ኃይለ ሚካኤልን ነፍስ እግዚአብሔር አምላክ በገነት ያሳርፍልን!!!

  ReplyDelete
 17. አሜን! በረከታቸው ይድረሰን።

  ReplyDelete
 18. amen! betam new yazenkut egziabher nefsachewen begenet yanurelenl! keberketachew yadelen!

  ReplyDelete
 19. Wow Dear D. Melaku

  What a exciting article. May GOD bless you and your family. If you don't write about this marvelous ABAT no body knows. EGZIABHERE KALE HIYWOT YASEMALIN Yageliglot zemenihin yarzimilin.

  መጋቤ ሐዲስ የኔታ ኃይለ ሚካኤል በአካባቢው የነበሩትን ድብቅ ባዕድ አምልኮዎች ነቅለው ያጠፉ፣ ብዙ የሌላ እምነት ተከታዮችን አስተምረው ያጠመቁና በተለይ ታላላቅ ሸሖች ሳይቀር መጥተው ግራ ያጋባቸውን ሲጠይቋቸው ከዚያው ከቁራኑ ጀምረው ያስረዱ የነበሩ ብዙዎችንም በስውር ወደ ክርስትናና ወደ ምናኔ ከመሩ ጥቂት አባቶች አንዱ ነበሩ፡፡

  ReplyDelete
 20. amen, it is really touchy!

  ReplyDelete
 21. Amen Abatachin hulem bereketewet yideribin Ayileyen ERSEWEN SINASITAWIS HOD YIBSENAL atisnagne melak yilakilien yetetekutinim abat yersewe bereket etif dirib hono werdo Ende nebiyu elsa yadrigilin!!!!!

  ReplyDelete
 22. ከብፁእ አባታችን በረከት ያሳትፈን:

  ReplyDelete
 23. Hi Dn.

  I was ameused and emotional when I read the story. So I wanted to speared the story. To this effect I am planning to publish this article in a magazine for a church in South Australia, Adelaide (Fund raising magazine for Hamere-Nohi Kidanemihret church). We will acknowledge the source, I hope this will be ok. If you have any objection please send me a message on fikishb@yahoo.com.

  Regards!

  ReplyDelete
 24. Dear Dn. Melaku,

  I was wondering if you would be willing to let us publish this article in a magazine for a church in South Australia for fund raising purpose. It is Hamere -Nohi Kidane Mihiret Church. We will acknowledged the source. Should you have any objection please communicate me via fikishb@yahoo.com.

  Regards!

  ReplyDelete
  Replies
  1. እኔ በጣም ነው ያዘንኩት ብፁኅ አባታችን ለመጨረሻጊዜ ያኋቸው በ2000 ዓም ነበር በ2004 ላገኛቸው ሄጀ አልተሳካልኝም ነገር ግን በዚህ አመት ለመርቖሪዎስ ለማግኘት ነበር ነገር ግን የእግዚአብሄር ፈቃድ አልሆነም ኘፍሳቸውን ይማር፡፡

   Delete
  2. እኔ በጣም ነው ያዘንኩት ብፁኅ አባታችን ለመጨረሻጊዜ ያኋቸው በ2000 ዓም ነበር በ2004 ላገኛቸው ሄጀ አልተሳካልኝም ነገር ግን በዚህ አመት ለመርቖሪዎስ ለማግኘት ነበር ነገር ግን የእግዚአብሄር ፈቃድ አልሆነም ነፍሳቸውን ይማር፡፡

   ደሳለኝ መ.

   Delete