Thursday, December 20, 2012

የብሕትውና(የምንኩስና) ኑሮ - ክፍል 3

ምንኵስና በኢትዮጵያ
ከ4ኛው መ/ክ/ዘ በፊት
ሥርዓተ ምንኵስና ወደ ሀገራችን የገባው በኢትዮጵያ በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን አጋማሽ በአባ ጳኩሚስ ዘመን ቢሆንም የብሕትውና ኑሮ ግን በሀገራችን ከዚያም ቀድሞ እንደነበረ የሚጠቁሙ አንዳንድ መረጃዎች አሉ፡፡
አባ አሞንዮስ፡- ሥርዓተ ምንኵስና ወደ ኢትዮጵያ ከመግባቱ በፊት አሞንዮስ የተባሉ ባሕታዊ በተንቤን ቆላ ደብረ አንሣ በተባለው በረሃ በጾም በጸሎት ተወስነው ይኖሩ ነበር፡፡


አባ ዮሐኒ፡- በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን መግቢያ ላይ በትግራይ ተንቤን አውራጃ በሀገረ ሰላም ቀበሌ ተወለዱ፡፡ በዚያን ዘመን ሥርዓተ ምንኵስና ወደ ኢትዮጵያ ባይገባም አበው በምናኔ በበረሃ ይኖሩ ነበር፡፡ የአባ ዮሐኒ ቤተሰቦች ድሆች ስለነበሩ አባ አሞንዮስ ወስደው አሳደጓቸው፡፡ ካደጉ በኋላም ከአባ አሞንዮስ ተለይተው ወደ በረሃ ለብቻቸው በመውረድ በተጋድሎ ሲኖሩ ከቆዩ በኋላ በተወለዱ በ3ዐ ዓመታቸው ኀዳር 5 ቀን እግዚአብሔር ወደ ብሔረ ሕያዋን በመላእክት እጅ እንደወሰዳቸው ገድለ አባ ዮሐኒ ይገልጣል፡፡
    ሥርዓተ ምንኵስና በኢትዮጵያ ለመስፋፋት የበቃው በሁለት ዓይነት መንገድ ነው፡፡
       1- ከውጭ ወደ ሀገራችን በገቡ ቅዱሳን
      2-በኢትዮጵያውያን ቅዱሳን

ወደ ሀገራችን የገቡ ቅዱሳን፡
ከመካከለኛው ምሥራቅ፣ ከታናሸ እስያና ከሮማ ግዛት ወደ ሀገራችን በልዩ ልዩ ምክንያት ገብተው ሥርዓተ ምንኵስናን ያስፋፉ ገዳማትን የገደሙ አበው አያሌ ሲሆኑ ዋና ዋናዎቹ የሚከተሉት ናቸው፡፡
አባ ሊባኖስ፡-
በቁስጥንጥንያ አጠገብ ሩም በተባለች ቀበሌ ተወለደ፡፡ በልጅነቱ በዲቁና ሲያገለግል ቆይቶ ወደ ግብፅ በመምጣት ሥርዓተ ምንኵስና ተፈጸመለት፡፡ ወደ እስክንድርያ በመጓዝም እስከ ቁምስና ማዕረግ የደረሰ አባት ነው፡፡ በ486 ዓ.ም. ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት 8ዐ ዋሻዎች አንፆ ሥርዓተ ምንኵስናን አስፋፍቶ በዐፄ ገብረ መስቀል ዘመነ መንግሥት ጥር 3 ዐርፏል፡፡
ተስዐቱ ቅዱሳን
ተስዐቱ ቅዱሳን
በኬልቄዶን ጉባዔ የልዮን ጦማር ያልተስማሙትን ኦርቶዶክሳውያን አባቶች ሮማውያን በግፍ በሚያሳድዱበት ዘመን ከሮም፣ ከታናሽ እስያና ከመካከለኛው ምሥራቅ ወደ ግብፅ በመውረድ በዚያም ሥርዓተ ምንኵስናን ፈጽመው፣ ተምረው፣ በአንድነት በ48ዐ ዓ.ም. ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ሥርዓተ ምንኵስናን የበለጠ ያስፋፉ አበው ናቸው፡፡ ገዳማቱ እስከዛሬ ድረስ ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ዘጠኝ ቅዱሳንም የሚከተሉት ናቸው፡፡

ስም
ገዳም
የዕረፍት ቀን
ሀገራቸው
አባ አሴፍ
አባ አረጋዊ
አባ አፍጼ
አባ ሊቃኖስ
አባ ገሪማ
አባ ጉባ
አባ ይምዓታ
አባ ጰንጠሌዎን
አባ ጽሕማ
ብኀዛን (አህስአ)
ደብረ ዳሞ
የሃ/ዬሐ
ደብረ ቆናጽል
መዱራ
ገርዓልታ
ገርርዓልታ
አኵስም (አጠገብ)
ጼዴንያ
መጋቢት 11
ጥቅምት 14
ግንቦት 12
ኀዳር 21
ሰኔ 29
ግንቦት 29
ጥቅምት 23
ጥቅምት 6
ጥር 16
ቂሣርያ
ሮም
እስያ
ቁስጥንጥንያ
ሮም
ኪልቂያ
ቆሲያ
ሮም
አንጾኪያ

አባዮሐንስ (ዘጐንድተ/ሃይማኖት)
አቡነ ዮሐንስ (ዘጐንድተ/ሃይማኖት)
የትውልድ ሀገራቸው ፍልስጥኤም ሲሆን ወደ ኢትዮጵያ የገቡት በ11ዐዐ ዓ.ም. ነው፡፡ አባ ዮሐንስ በተለይ ከአፋር ክልል ደብረ አዘሎ፣ ደብረ ደንኖ፣ ደብረ ፀገ፣ ደብረ ገሮ፣ ደብረ አሳራ በተባሉ ሥፍራዎች ሥርዓተ ምንኵስናን አስፋፍተዋል፡፡ በመጨረሻም በለሳ በረሃ ወርደው ጐንድ ገዳምን በመመሥረት ሐምሌ 29 ቀን በተወለዱ በ5ዐዐ ዓመታቸው በ15ዐዐ ዓ.ም. ዐርፈዋል፡፡

ጻድቃን
ተሰዐቱ ቅዱሳን ወደ ኢትዮጵያ ከመምጣታቸው በፊት በግልና በኀብረት እየሆኑ አያሌ መነኰሳት ወደ ሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ገብተው ነበር፡፡ እነዚህም ቅዱሳን (ጻድቃን) እየተባሉ ሲሆን በቅርቡ መጽሐፈ ገድላቸው እስከ ተገኘበት ጊዜ ድረስ ስለነርሱ የሚታወቀው እጅግ ጥቂት ነበር፡፡ እነርሱም በኤርትራ ቆላማው ሥፍራ ሥርዓተ ምንኵስናን ያስፋፉ መሆናቸው ታውቋል፡፡
አርባ ሐራ፡-
አቡነ ሐራ የተባሉት ቅዱስ በዘጠነኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከግብፅ ወደ ኢትዮጵያ በመግባት በአኵስም ከቆዩ በኋላ አያሌ መጻሕፍት እና ንዋያተ ቅድሳት ይዘው ወደ መንዝ ማማ ምድር በመምጣት በዋሻ ውስጥ ተቀመጡ፡፡ የዮዲት ዘመን ካለፈ በኋላ ደግሞ 4ዐ ቅዱሳን ከግብፅ ከገዳመ አስቄጥስ መጥተው ከአቡነ ሐራ ጋር 4 ሰዓት የሚያስኬድ ዋሻ ፈልፍለው ማኀበረ መነኰሳት አቁመው መኖር ጀመሩ፡፡
ከዚህም መካከል 2ዐዎቹ ዞረው ሲያስተምሩ 2ዐዎቹ ደግሞ የተግባር ቤቱን ሥራ ያከናወኑ ነበር፡፡
በአካባቢውም ትምህርተ ወንጌልንና ሥርዓተ ምንኵስናን ካስፋፉ በኋላ አስቀድመው 4ዐው ቅዱሳን በኋላም አቡነ ሐራ በተወለዱ በ22ዐ ዓመታቸው በ11ዐዐ ዓ/ም ዐረፉ፡፡ የእርሳቸውንም ፈለግ አባ ፍሬ ሠናይ የተባሉ አባት ተከተሏቸው፡፡ ይህም ሥፍራ ዛሬ አርባራ መድኃኔዓለም ገዳም በመባል ይታወቃል፡:

በአሁኑ ወቅት ይህ ቦታ በተለያየ አፅፍ የተከፈኑ እና የተገነዙበትም ማሠሪያ ክር በእጃቸውና በእግራቸው ጣት ላይ የሚታይ ብዙ አፅሞች ይገኙበታል፡፡ ምንም እንኳን ዋሻው በአፅም የተሞላ ቢሆንም ከአካባቢው የሚወጣው መዓዛ ግን ከሙታን መንደር የሚገኝ መጥፎ ሽታ ሳይሆን (አልባብ አልባባ) የሚል መልካም መዓዛ ነው፡፡
የአካባቢው አረጋውያን እንደሚናገሩት ከሆነ ከኢጣሊያ ፋሺስት ወረራ በፊት ዘወትር የማኀሌት÷የከበሮና የዕልልታ ድምፅ ይሰማበት ነበረ፡፡ በተጨማሪም እጅግ ግዙፍ የሆነ ነጭ አሞራ እየበረረ ወደ ዋሻው ሲገባ ማየት የዘወትር ክስተት ነበረ፡፡ ከዚያ ወዲህ ግን ይህ ነገር ብዙም አይታይም፡፡
ቦታውን ከአካባቢው ምእመናን ጋር የሚያገናኘው ሌላው ነገር ደግሞ መሬት ሰብል እንዳትሰጥ ሰብል አጥፊ ተባይ ሲነሣ፣ እንስሳቱ ወተት መስጠታቸውን ሲቀንሱ ገበሬዎቹ አፅሞቹ ካረፉበት ቦታ አፈሩን በመዝገን በማሳቸው ላይ ይበትናሉ፤ እንስሳቱንም ያሻሹበታል፡፡ እንደ እምነታቸውም እንደሚያደርግላቸው በየዓመቱ ጥር 13 ቀን የሚገባው የእንስሳትና የሰብል ውጤት ምሥክር ነው፡፡ ከዋሻው የሚወጣው መልካም መዓዛም አሁንም ያልተቀየረ መሆኑን ሄዶ የሚመለከት ምሥክር ነው፡፡
አባ ኖብ
ትውልዳቸው በሶሪያ ሲሆን ወደ ኢትዮጵያ ወጥተው ከአቡነ ሳሙኤል ዘዋልድባ ጋር ተገናኙ፡፡ የኢትዮጵያውያንን ቋንቋና ባሕል ካጠኑ በኋላ በትግራይ ተንቤን ፀፀራ ወረዳ ከሚገኘው ዋሻ ላይ ቤተ ክርስቲያን ተክለው ገዳም መሠረቱ፡፡ ከዚያም ቀጥለው በመላ ኢትዮጵያ በመዘዋወር ገዳማትን መሥርተው በ11ዐዐ ዓ.ም. ኀዳር 8 ቀን ዐረፉ፡፡
አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ
ትውልዳቸው በግብፅ ሲሆን ገና በሕፃንነታቸው በልዑል እግዚአብሔር ፈቃድ በ11ዐዐ ዓ.ም. ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ሥርዓተ ምንኵስናን ያስፋፉ አባት ናቸው፡፡ እግዚአብሔር በሰጣቸው የ562 ዓመት ዕድሜ አያሌ ገዳማትን የገደሙ ሲሆን በተለይም የዝቋላና የምድረ ከብድ ገዳማት እስከዛሬ የፀኑ ናቸው፡፡
በኢትዮጵያ የምንኵስናና የገዳማት ታሪክ ውስጥ ከ3ኛው - 12ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ያለው ጊዜ በአብዛኛው ከውጭ በመጡ አበው ሥርዓተ ምንኵስና የተስፋፋበት ሲሆን ከ12ኛው-15ኛው ያለው ደግሞ ከመላ ኢትዮጵያ በተነሡ አበው ቅዱሳን ሥርዓተ ምንኵስናና የገዳማት ትክል ከሰሜን ወደ ምዕራብ፣ ምሥራቅና ደቡብ የተስፋፋበት ወቅት ነው፡፡
ዋቢ
1.    ትንሣኤ ቁ.99/1978
2.    ገድለ አባ ሊባኖስ
3.    ገድለ አባ ዮሐንስ
4.    ዜና መንዝ
5.    የአንኰበር መሳፍንት የታሪክ መጽሐፍ
6.    ትንሣኤ ቁ.11/79
7.    ትንሣኤ ቁ.22/80
8.    Conti Rossini, steria PL.XLIV
9.    ሉሌ መላኩ፣ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ አ.አ 1986
10. አባ ጎርጎርዮስ፤ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ በዓለም መድረክ
11. አባ ጎርጎርዮስ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ
ሐመር መጽሔት




12 comments:

  1. Kala hiwot yasemalin.

    ReplyDelete
  2. እግዚአብሔር ይስጥህ! ተክልዬን ደግሞ ከ አቡነ ገብረመንፈስ ቅዱስ ቀጥሎ ብትገልጻቸው ጥሩ ነበር በዬ አስባለሁ፡፡ ለማንኛውም ስለ ኢትዮጵያውያን ቅዱሳን ብዙ መጽሀፍት ብዙ የሚሉት ያለ ይመስለኛልና እባክህ ስለነሱ በደንብ አክልበት...

    ReplyDelete
  3. Kale hiwot yasemalin. Betene beselam yitebikilin!

    ReplyDelete
  4. If you have the resources, please give us the detailed account of the life of the saints. God bless you.

    ReplyDelete
  5. እግዚአብሔር እድሜና ጤና ይስጠህ

    ReplyDelete
  6. khy. I have a question not related to this article though. is there any way I can ask you?

    ruhama

    ReplyDelete

  7. አምላከ ዋልድባ ኢታርምም በክልኤ፡ወኢትጸመም ይእዜ፡
    አምጣነ ጊዜነ ኮነ እንተ አራዊት ጊዜ።

    ትርጉም:-

    የዋልድባ አምላክ ሆይ በሁለት ነገር ዝም አትበል አሁንም ቸል አትበል፡
    ጊዜአችን የአውሬዎች ጊዜ ሆኗልና።




    http://taborbetekine.blogspot.de/2012/12/home.html

    ReplyDelete
  8. አምላከ ዋልድባ ኢታርምም በክልኤ፡ወኢትጸመም ይእዜ፡አምጣነ ጊዜነ ኮነ እንተ አራዊት ጊዜ።

    ReplyDelete
  9. ቃለ ህወይት ያሰማልን.
    የአገልግሎት አድሜ ያርዝምልን.

    ReplyDelete
  10. "የአካባቢው አረጋውያን እንደሚናገሩት ከሆነ ከኢጣሊያ ፋሺስት ወረራ በፊት ዘወትር የማኀሌት÷የከበሮና የዕልልታ ድምፅ ይሰማበት ነበረ፡፡ በተጨማሪም እጅግ ግዙፍ የሆነ ነጭ አሞራ እየበረረ ወደ ዋሻው ሲገባ ማየት የዘወትር ክስተት ነበረ፡፡ ከዚያ ወዲህ ግን ይህ ነገር ብዙም አይታይም"

    I have seen many documentary videos about about this monastry. All said that everything is the same up this date. So please check your references and edit this part. God bless you!

    ReplyDelete
  11. እግዚአብሄር ይስጥልን ዲ/ን ምን አልባት "ዜና መንዝ" ብለህ ዋቢ ያደረግከዉን መጸሃፍ እንዴት እንደማገኘዉ ብትተባበረኝ



    ReplyDelete