Monday, April 30, 2012

ሊቀ ሰማዕታት ቅዱስ ጊዮርጊስ


ሰማዕት ማለት ምስክር ማለት ሲሆን በሃይማኖት ምክንያት የተገደለ፣ መከራ የደረሰበት ሰማዕት ይባላል። (ሐዋ.22፡20) የመጀመሪያዎቹ የሐዲስ ኪዳን ሰማዕታት ሐዋርያትና አርድዕት ናቸው።
ቅዱሳን ሰማዕታት የሚባሉት “እግዚአብሔርን ካዱ ለጣዖት ስገዱ” ሲባሉ “እግዚአብሔርን አንክድም ለጣዖት አንሰግድም” በማለት በዓላውያን ነገሥታት ፊት ቀርበው ሳያፍሩና ሳይፈሩ ስለጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የባህርይ አምላክነት የመሰከሩ ናቸው። በዚህም ምክንያት ተዘርዝሮ የማያልቅ የመከራ ዓይነት ተቀብለው ለፈጣሪያቸው ክብር ሲሉ ደማቸውን ያፈሰሱ፣ አጥንታቸውን የከሰከሱ፣ ሕይወታቸውን ያጡ ናቸው።
በእሳት ተቃጥለዋል፣ በውኃ ተቀቅለዋል፣ በሰይፍ ተመትረዋል፣ በመጋዝ ተተርትረዋል፣ በመንኩራኩር ተፈጭተዋል (መንኩራኩር የሚባለው በዘመነ ሰማዕታት የነበረ ዘመናዊ የወፍጮ መሳሪያ ነው።)፣ እንደከብት ቆዳቸው ተገፏል፣ ወደጥልቅ ባህር ተጥለዋል። በዚህ ሁሉ መከራ ውስጥ ከሃይማኖታቸው አላፈገፈጉም፤ እንዲያውም ሌሎች “እኔ በእነርሱ አምላክ አመልካለሁ” እንዲሉ አድርገዋቸዋል።

ዘመነ ሰማዕታት የሚባለው በአርማንያ 40 ዘመን ሲሆን ብዙ ቅዱሳን ሰማዕትነትን ተቀብለውበታል። ከኢትዮጵያም 1600 ክርስቲያኖች በቀን “ይህ ሰማዕትነት አያምልጠን” በማለት ሄደው ተሰውተዋል። በዘመኑ የነበሩት አረማውያን ነገሥታት ዲዮቅልጥያኖስ፣ መክስምያኖስ፣ ድርጣድስ፣ እለእስክንድሮስ፣ በኡልያኖስ፣ በፋርማህ እጅ የተሰዉ ነበሩ።
v ማቴ.10፡28 “ሥጋንም የሚገድሉትን ነፍስን ግን መግደል የማይቻላቸውን አትፍሩ፤ ይልቅስ ነፍስንም ሥጋንም በገሃነም ሊያጠፋ የሚቻለውን ፍሩ።”
v ዕብ.11፡34 – 38 “የአንበሶችን አፍ ዘጉ፥ የእሳትን ኃይል አጠፉ፥ ከሰይፍ ስለት አመለጡ፥ ከድካማቸው በረቱ፥ በጦርነት ኃይለኞች ሆኑ፥ የባዕድ ጭፍሮችን አባረሩ።ሴቶች ሙታናቸውን በትንሣኤ ተቀበሉ፤ ሌሎችም መዳንን ሳይቀበሉ የሚበልጠውን ትንሣኤ እንዲያገኙ እስከ ሞት ድረስ ተደበደቡ፤ሌሎችም መዘበቻ በመሆንና በመገረፍ ከዚህም በላይ በእስራትና በወኅኒ ተፈተኑ፤በድንጋይ ተወግረው ሞቱ፥ ተፈተኑ፥ በመጋዝ ተሰነጠቁ፥ በሰይፍ ተገድለው ሞቱ፥ ሁሉን እያጡ መከራን እየተቀበሉ እየተጨነቁ የበግና የፍየል ሌጦ ለብሰው ዞሩ፤ዓለም አልተገባቸውምና በምድረ በዳና በተራራ፥ በዋሻና በምድር ጕድጓድ ተቅበዘበዙ።”
አዲስ አበባ መናገሻ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን
ሊቀ ሰማዕታት ቅዱስ ጊዮርጊስ   በጥር 20 ቀን በ277 ዓ.ም ተወለደ። ሀገሩ ፍልስጤም ሲሆን ልዩ ስሟ ልዳ ይባላል። ጊዮርጊስ ማለት ኮከብ፣ ብሩህ፣ ሐረገወይን፣ ፀሐይ ማለት ነው። አባቱ ዞሮንቶስ (አንስጣስዮስ) ይባላል ከልዳ መኳንንት ተሹሞ ይኖር ነበር፤ እናቱ ቴዎብስታ (አቅሌስያ) ትባላለች። ማርታና እስያ የሚባሉ እህቶች ነበሩት። 10 ዓመት ሲሞላው አባቱ ስለሞተ ሌላ ደግ ክርስቲያናዊ መስፍን ከቤቱ ወስዶ አሳደገው። በጦር ኃይልም አሠለጠነው። 20 ዓመት ሲሞላው የ15 ዓመት ልጅ ሊያጋቡት ሲሉ እግዚአብሔር የመስፍኑን ነፍስ ወስደ፤ ቅዱስ ጊዮርጊስም ወደ ቤሩት ሄደ።
v  በቤሩት ደራጎን ን ያመልኩና ሴት ልጃቸውን ይገብሩለት ነበርና በኃይለ መስቀል ድል ነስቶት ህዝቡን ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር አስገብቷቸዋል።
v  ወደፋርስ ቢመለስ ዱድያኖስ ሰባ ነገሥታት ሰብስቦ ሰባ ጣዖታት አቁሞ ሲሰግድ ሲያሰግድ ቢያገኛቸው ለሃይማኖቱ ቀናዒ ነውና ከቤተመንግስቱ ገብቶ “እኔ ክርስቲያን ነኝ በኢየሱስ ክርስቶስ አምናለሁ” አለው። እርሱም ማንነቱን ከተረዳ በኋላ  “አንተማ የኛ ነህ በ10 አህጉር ላይ እሾምሃለሁ የኔን አምላክ አጵሎንን አምልክ” አለው። ቅዱስ ጊዮርጊስም “ሹመት ሽልማትህ ለአንተ ይሁን እኔ አምላኬ ኢየሱስ ክርስቶስን አልክድም” አለ። በዚህ ጊዜ እጅግ ተናዶ መከራን አጸናበት እርሱ ግን “ይህን ከሀዲ እስካሳፍረው ድረስ ነፍሴን አትውሰድ” በማለት እግዚአብሔርን የለመነና እንደጸሎቱ የተደረገለት። በእምነቱም ጽናት የሰው ልጅ ሊሸከም የማይችለውን መከራ የተቀበለ ቅዱስ አባት ነው። ከእነዚህም መከራዎች ውስጥ፡-
1.      በእንጨት አስቀቅሎ ሥጋውን በመቃን አስፈተተው
2.     ረጃጅም ችንካሮች ያሉበት የብረት ጫማ አጫምቶት ሂድ አለው። ቅዱስ ሚካኤልን ልኮለት ፈውሶታል።
3.     በሰባ (70) ችንካር አስቸንክሮ በእሳት አስተኩሶ አናቱን በመዶሻ አስቀጥቅጦ በሆዱ ላይ የደንጊያ ምሰሶ አሳስሮ እንዲያንከባልሉት አደረገ።
4.     ሥጋውን በመጋዝ አስተልትሎ ጨው ነስንሶበት ሥጋው ተቆራርጦ ወደቀ። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመንፈቀ ሌሊት በእጁ ዳስሶ “ገና 6 ዓመት ለስሜ ትጋደላለህ፣ 3 ጊዜ ትሞታለህ፣ በ4ኛው ታርፋለህ።” አለው።
5.     ዱድያኖስ ደንግጦ “የሚያሸንፍልኝ ቢኖር ወርቅ እሰጠዋለሁ” ቢል አትናስዮስ የተባለ መሰርይ ከንጉሱ ላምን በጆሮዋ ሲያንሾካሹክባት ለሁለት ተሰንጥቃ ገድሏት ፈቃድን ተቀበለ። ሆድ በጥብጦ አንጀት ቆራርጦ የሚገድል መርዝ ቀምሞ አስማተ ሰይጣን ደግሞ ሰጠው። ቅዱስ ጊዮርጊስ ግን ስመ እግዚአብሔርን ጠርቶ ቢጠጣው እንደ ጨረቃ ደምቆ  እንደ አበባ አሸብርቆ ተገኝቷል። ጠንቋዩም ማረኝ ብሎት ከመሬት ውሃን አፍልቆ ወደ ጌታችን ቢያመለክት ሐዋርያው ቶማስን በመንፈስ መጥቶ አጥምቆት በሰማዕትነት አርፏል።
6.     በመንኮራኩር አስፈጭቶ ከትልቅ ጉድጓድ ጥሎት ደንጊያ ዘግቶበት አትሞበት ሄዷል። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ  የተፈጨውን ሥጋ በእጁ ዳስሶ መንፈሱን መልሶ አንስቶታል፤ ተመልሶም “አምላኬ ከሞት አዳነኝ” ብሏቸዋል።
7.     በብረት አልጋ አስቸንክሮ ከበታቹ እሳት አንድዶበታል። እሳቱም ደሙ ሲንጠባጠብ ጠፍቷል።
8.     ዱድያኖስ “ኢየሱስ አምላክ መሆኑን አሳየኝ” ቢለው የለመለሙትን ዕፅ አድርቆ፣ የደረቁትን አለምልሞ፣ ከሞቱ 430 ዓመት የሆናቸውን ሙታንን አስነስሰቶ አሳይቶታል። ነገር ግን ልቡ ክፉ ነውና በረሀብና በጽም ይሙት ብሎ ምንም ከሌላት መበለት ቤት አሳስሮታል። እርሷም የሚቀመስ ስትፈልግ ቤቷን በእህል አትረፍርፎ የታሰረበት ግንድ አፍርቶ ልጇ ጆሮው የማይሰማ ነበርና ፈውሶላት መበለቲቷን ከነልጆቿ አጥምቆ ቅዱስ ሚካኤል ከእስራቱ ፈትቶት ተመልሷል።
9.     ዳግም በመንኩራኩር ፈጭታችሁ ደብረ ይድራስ ወስዳችሁ ዝሩት ብሎ አስፈጭቶ ሥጋውን ቢዘሩት ሥጋው ያረፈበት ሳር፣ ቅጠሉ፣ ደንጊያው፣ እንጨቱ  ሁሉ “ጊዮርጊስ ቅዱሱ ለእግዚአብሔር፣ ጊዮርጊስ ሰማዕቱ ለእግዚአብሔር፣” እያሉ አመስግነዋል። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ለሦስተኛ ጊዜ ከሞት አስነስቶታል። ሔዶም “አምላኬ ከሞት አዳነኝ” አላቸው። ጭፍሮቹ ደንግጸው ከእግሩ ስር ወደቁ። ከመሬት ውሃ አመንጭቶ ቅዱስ ዮሐንስ አጥምቋቸዋል።
10.    “ንጉሡ ልሹምህ ለአጵሎን ስገድ” ብሎ ቢለምነው እሺ ብሎ ገብቶ ሲጸልይ የንጉሱ ሚስት እለእስክንድርያ “ምን እያልክ ነው?” ብትለው አስተምሯት አሳምኗታል። ሲነጋ ንጉሱ በአዋጅ ህዝብን አሰብስቦ “ጊዮርጊስ ለጣዖቴ ሊሰግድ ነው’ ብሎ በተሰበሰበ ህዝብ መካከል አንድን ብላቴና (የመበለቷን ልጅ) “የክርስቶስ ኢየሱስ አገልጋይ ጊዮርጊስ ይጠራሃል” በል ብሎ ወደጣዖቱ ቢልከው ጣዖቱ ላይ ያደረው ሰይጣን እየጮኸ ቅዱስ ጊዮርጊስ ያለበት ቦታ መጣ፤ አምላክ አለመሆኑን አናዞት መሬት ተከፍታ እንድትውጠው አደረገ። ብዙ ሰዎች ይህንን ተዓምር አይተው አመኑ። ንጉሱን ሚስቱ እንዲመለስ ብትነግረው በአደባባይ አሰቅሎ አሰይፏት ሞታለች ደሟን ጥምቀት አድርጎላት ሰማዕት ሆናለች።
11.     በመጨረሻም በሰይፍ እንዲመተር አስደረገ። ቅዱስ ጊዮርጊስም ከጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቃልኪዳን ተገብቶለት በ27 ዓመቱ በሚያዝያ 23 ቀን በ9፡00 ሰዓት ሰማዕት ሆኗል። አንገቱ ሲቆረጥ ውሃ፣ ደም እና ወተት ወጥቷል።
ከሊቀ ሰማዕታት ቅዱስ ጊዮርጊስ ረድኤት በረከት ይክፈለን

17 comments:

  1. ዲያቆን መላኩ
    የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ዕውቀቱን ያብዛልህ።
    ሥራህን ይባርክ።
    ቃለ ሕይወት ያሰማልን።

    የእናቱ የቅድስት ድንግል ማሪያም አማላጅነት አይለይህ።
    አይለየን።
    አሜን።

    ReplyDelete
  2. አሜን!!! ቃለ ሒወት ያሰማልን። የፈረሰኛው ሰማእት የቅዱስ ጊዮርጊስ ረድኤትና ምልጃ አይለይህ።

    ReplyDelete
  3. Amen Amne wendemachen betame newe yemenamesgenewe kale heyewet yasemalen

    ReplyDelete
  4. amelaka gioregis yeredah

    ReplyDelete
  5. ቃለ ሕይወት ያሰማልን።
    አሜን።
    አሜን።
    አሜን።
    05/01/2012@10:06

    ReplyDelete
  6. Kale hiwot yasemalin!

    ReplyDelete
    Replies
    1. Amen kale hiwot yasemalen yeagelglot zemenehen yibarkle!!!!!!!!

      Delete
  7. ቃለ ሕይወት ያሰማልን።
    አሜን።
    አሜን።
    አሜን።

    ReplyDelete
  8. kalehiwoten yasemalen Mengistesemayaten yawreselen! Amen!

    ReplyDelete
  9. Thank you

    Kale Hiwot Yasemmaline.

    Amen.

    ReplyDelete
  10. ቃለሕይወት ያሰማልን ዲያቆን መልኣኩ እዘዘው
    እግዚኣብሔር የኣገልግሎት ዘመንህን ያርዝምልን!!!!ኣሜን
    ልብ ብለህ መልእክቴን ብታየው እና ያልኩህን ብታደርግልኝ ደስ ይለኛል
    እስቲ የቅዱስ ኣቡነ ኣረጋዊ ገድል ወይም ታሪክ ጻፍልን ፈልጌ ኣጣሁኝ
    ትልቅ ኣባት ሲሆኑ ግን ሰፊ ጽሁፍ ላገኝ ኣልቻልኩም
    እጠብቃለሁ እግዚኣብሔር ካንተ ጋር ይሁን!!!!ኣሚን
    መርሃዊ ከመቀሌ

    ReplyDelete
  11. Amen. Thank you.

    ReplyDelete
  12. thanks God bless your time and life

    ReplyDelete
  13. አሜን፣ ቃለ ሕይዎት ያሰማልን፣ ተስፋ መንግስተ ሰማያትን ያውርሥልን።

    ReplyDelete
  14. አሜን፣ ቃለ ሕይዎት ያሰማልን፣ ተስፋ መንግስተ ሰማያትን ያውርሥልን።

    ReplyDelete