Wednesday, December 28, 2011

ቅዱስ ገብርኤል



በስመአብ ወወልድ ወመንፈስቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን

እንኳን ለቅዱስ ገብርኤል በዓል በሰላም አደረሳችሁ

ከሰባቱ ሊቃነ መላእክት አንዱና በእግዚአብሔር ፊት የሚቆመው ታማኝ መልአክ ቅዱስ ገብርኤል ነው፡፡ በተረዳኢነቱና በአማላጅነቱ በክርስቲያኖች ዘንድ ይወደዳል፡፡ ምክንያቱም ያዘኑትን ለማጽናናት የምሥራች ለመንገር ከእግዚአብሔር ወደ ምእመናን ይላካልና፡፡
ገብርኤል ማለት የእግዚአብሔርን ልጅ የሚመስል ጌታና አገልጋይ ማለት ነው፡፡ ብርሃናዊ መልአክ ቅዱስ ገብርኤል፣ ቅዱሳን ሰማእታት ገድላቸውን እንዲፈጽሙ እሳቱንና ስለቱን ተሳቀው ወደ ኋላ እንዳይመለሱ ይረዳቸዋል፡፡
ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያናችን የቅዱሳን መላእክትን ወርኃዊና ዓመታዊ በዓላቸውን በፀሎትና በምሥጋና ታከበራለች፤ በተለይ ታህሣሥ 19 ቀን የሚከበርበት ምክንያት ብርሃናዊ መልአክ ቅዱስ ገብርኤል ሠለሥቱ ደቁቅን ከዕቶነ እሳት ( ከነደደ እሳት ) ያዳነበት ዕለት በመሆኑ ነው፡፡
ቁልቢ ገብርኤል
በጣዖት ፍቅር እጅግ ከመጠን በላይ ልቡ ተቃጥሎ የነበረው የባቢሎን መሪ ናቡከደነጾር ቁመቱ ስድሳ ወርዱ ስድስት ክንድ የሆነውን የወርቅ ምስል አሰርቶ መኳንንቱን ሰብስቦ ሕዝቡ በሙሉ ለጣኦት እንዲሰግድ አዋጅ አወጀ፡፡ ያ ዘመን ለእግዚአብሔር ወዳጆች የፈተና ዘመን ነበር፡፡ አስመሳዮች ለጣኦት ሰገዱ ተረበረቡ፡፡ እውነተኛው አማኞች ግን በእግዚአብሔር ላይ ያላቸው እምነት ንጉሥ የወደደው ጊዜ የወለደው በሚል አስተሳሰብ አይለወጥም፡፡
በዚያ ፈታኝ ዘመን ነበር ሶስት ታማኝ የእግዚአብሔር ባለሟሎች የተገኙት፡፡ ንጉሡ ላቆመው ጣኦት ያልሰገደ ወደ እቶን እሳት ተጥሎ እንደሚሞት ቁርጥ ውሣኔው መሆኑን ወጣቶቹ በሚገባ ያውቁታል ግን ይህንን አልፈሩም፡፡ ንጉሥ ሆይ አምላካችንን በመካድ አንተ ላቆምከው ጣኦት አንሰግድም አሉት፡፡ ሶስቱ ወጣቶች የወሰዱት ይህ አቋም ለንጉሡ ታላቅ ራስ ምታትን ፈጠረ፤ ንጉሡም አገልጋዮቹን ጠርቶ እሳቱ ሰባት እጥፍ እንዲነድ ትዕዛዝ ሰጠ እሳቱም ሰባት እጥፍ ነደደ፡፡
ወዲያውኑ የንጉሡ አገልጋዮች አናንያን፣ አዛርያ፣ ሚሳኤልን እያንከበከቡ ወደ እቶን እሳት ወረወሯቸው ፡፡ ሠለስቱ ደቂቅ ከየት እንደመጣ ከማይታወቅ እንግዳ ጋር በመሆን በዕቶን እሳት ውስጥ ይንሸራሸሩ ጀመር፡፡ ይህ ተዓምራት ንጉሡንና መኳንንቱን አስገረመ ንጉሡም በዚህ ወቅት እነሆ እኔ በእሳቱ መካከል የሚመላለሱ አራት ሰዎች አያለሁ እሳቱ ምንም አላቆሰላቸውም አራተኛውም የአማልክትን ልጅ ይመስላል አለ፡፡
ጎንደር ደብረምህረት አቡን ቤት ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን 
ከጎሃ ሆቴል ተራራ ላይ ሲታይ

የነደደ እሳት ውስጥ ገብቶ ከመውጣት ባልተናነሰ መከራ ውስጥ ገብተው በቅዱስ ገብርኤል አማላጅነት ከሞተ ሥጋ ነፍስ ድነው እውነተኛ ምሥክርነታቸውን የሚሰጡ ብዙዎች ናቸው፡፡ በመልአኩ ሥም በፈለቀው ጠበል ተጠምቀው ደዌ የራቀላቸው እጅግ በርካታ ናቸው፡፡ በየዓመቱ በቁልቢና በቅዱስ ገብርኤል ስም በታነጹ አብያተ ክርስቲያናት የሚሰበሰበው ምዕመናን ሥዕለቱ የሰመረለት ልመናው የተሰማለት እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ ስለዚህ ለመላእክት አለቃ ለቅዱስ ገብርኤል የተሰጠውን ጸጋ ተረድተን የመልአኩን አማላጅነት በመጠቀም ልናከብረው  ይገባል፡፡
የመልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ረድኤት እና በረከት አይለየን - አሜን

6 comments:

  1. Dn."KALEHIWOTE YASEMALEN" Kemelaku eradete yakafelen!!!Berta Wondemia!!!

    ReplyDelete
  2. ቃለ ህይወት ያሰማልን

    ReplyDelete
  3. ቃለ ህይወትን ያሰማልን ዲያቆን!! የመላኩ የቅዱስ ገብርኤል አማላጅነት እና ተራዳኢነት አይለየን!!!

    ReplyDelete
  4. ቃለ ህይወት ያሰማልን።
    "ከየት እንደመጣ ከማይታወቅ እንግዳ ጋር" ማለት ግን ምንማለት ነዉ? የመጣዉም እሳቱን እንደ ዉሃ ያቀዘቅዝላቸው ዘንድ ከእግዚአብሄር ተልኮ ነዉ ይህም ይታወቃል:: ታዲያ "ከየት እንደመጣ ከማይታወቅ እንግዳ ጋር" መባሉ ምን ለማለት ነዉ? እባክዎ ያብራሩልን።

    ReplyDelete
  5. ገብርኤልየ ስደተኞች ልጆችህን አስብ:: በአማላጅነትህ እንታመን አለንና::ፎተግራፎን ስመለከት ሰፈሪ መንደሪ ታወሰኝ::

    ReplyDelete
  6. Amen!! Kale Hiwot yasemalin

    ReplyDelete