Thursday, November 3, 2011

ዮሐንስ ሐፂር


ዮሐንስ ሐፂር

ዮሐንስ ሐፂር በላይኛው ግብጽ ቴባን በምትባል መንደር በ339 ዓ.ም ተወለደ፡፡ ወደ ገዳም አስቄጥስ የገባው በልጅነቱ ሲሆን ያን ጊዜ አበምኔቱ አባ ባሞይ ይባል ነበር፡፡ አባ ዮሐንስ በተመሥጦው እና በታዛዥነቱ የታወቀ አባት ነበር፡፡ በመጀመርያው የአስቄጥስ ጥፋት ጊዜ ገዳሙን ትቶ ወደ ቁልዝም ተጓዘ፡፡ ያረፈውም በዚያ ነው፡፡
የዮሐንስ ሐጺርን ትምህርቶች ከዚህ እንደሚከተለው አቅርበነዋል ፡፡

1. የጠላቱን ከተማ ለመቆጣጠር የዘመተ ንጉሥ አስቀድሞ የውኃውን መንገድ ይዘጋል፣ የእህሉንም መግቢያ ይይዛል፡፡ ያን ጊዜ ጠላቶቹ ይራባሉ፣ ይጠማሉ፡፡ በመጨረሻም እጃቸውን ይሰጣሉ፡፡ የነፍስን ፆር ለማሸነፍም በተመሳሳይ መንገድ መጠቀም ይገባል፡፡ አንድ ሰው በጾምና በረኃብ ከጸና የነፍሱ ጠላቶች ይዳከማሉ፡፡

2. እኔ በትልቅ ዋርካ ሥር የተቀመጠንና አራዊት ሊጣሉት የመጣን ሰው እመስላለሁ፡፡ ሊቋቋማቸው እንደማይችል ከተረዳ ሸሽቶ ወደ ዛፉ በመውጣት ነፍሱን ያድናል፡፡ በእኔም የተፈጸመው ይኼው ነው፡፡ በበዓቴ ተቀምጬ ክፉ ሃሳቦች ሊቃወሙኝ ሲመጡ፣ ልቋቋማቸው እንደማልችል ባወቅኩ ጊዜ በጸሎት ወደ እግዚአብሔር ሸሽቼ እመሽጋለሁ፡፡ በዚያም ከጠላቶቼ ፍላፃ እድናለሁ፡፡

ዮሐንስ ሐፂር
3. መለወጥ የምትፈልግን ነፍስ በተመለከተ አባ ዮሐንስ እንዲህ አለ፡- በአንዲት ከተማ ውስጥ ብዙ ወዳጆች የነበሯት አንዲት አመንዝራ ሴት ነበረች፡፡ ከገዥዎቹ አንዱ ቀረባትና ‹መልካም ሴት ለመሆን ቃል ግቢልኝና አገባሻለሁ› አላት፡፡ እርሷም ቃል ገባችለትና ተጋቡ፡፡ ወደ ቤቱም ወሰዳት፡፡ የቀድሞ አፍቃሪዎቿ ያቺን ሴት ፈለጓት፣ እርስ በርሳቸውም ‹ያ ልዑል ወደ ቤቱ ወስዷታል፤ ወደ ቤቱ ብንሄድ ይቀጣናል፡፡ ነገር ግን በጓሮ በኩል እንሂድ፣ ለርሷም እናፏጭላት፣ የፉጨቱን ድምፅ ስትሰማ ከድርሱ ወርዳ ወደኛ ትመጣለች፣በዚህም ያለ ችግር እናገኛታለን› ተባባሉ፡፡ ወደ ቤቷም ጓሮ ተጉዘው ያፏጩ ጀመር፡፡ እርሷ ግን የፉጨቱን ድምፅ ስትሰማ ጆሮዎቿን ደፈነች፡፡ ወደ ውስጣዊው እልፍኝም ገባች፡፡ በሩንም ጥርቅም አድርጋ ዘጋች፡፡ ይህቺ ሴት የኛ ነፍስ ምሳሌ ናት፡፡ ወዳጆቿ የተባሉም ፈተናዎቿ ናቸው፤ ገዥ የተባለውም ክርስቶስ ነው፣ እልፍኝ የተባለውም ዘለዓለማዊው ቤት ነው፡፡ እነዚያ የሚያፏጩት ክፉዎች አጋንንት ናቸው፤ ነገር ግን ነፍስ ሁልጊዝም በክርስቶስ አምባነት ትሸሸጋዋለች፡፡

4. አባ ዮሐንስ ልቡናው ከእግዚአብሔር ጋር ስለነበረ ምድራዊ ነገሮችን ይዘነጋ ነበር፡፡ አንድ ቀን አንድ ወንድም ቅርጫት ሊወስድ ወደ አባ ዮሐንስ በኣት መጣ፡፡ አባ ዮሐንስም ምን ፈልጐ እንደሆነ ጠየቀው፡፡ ያም ወንድም ‹ቅርጫት ፈልጌ ነው› አለው፡፡ አባ ዮሐንስ ወደ በኣቱ ተመለሰና ዘንግቶት ወደ ሽመና ሥራው አመራ፡፡ ጥቂት ቆይቶ ያ ወንድም አንኳኳ፣ አባ ዮሐንስም ወጥቶ ‹ምን ፈልገህ ነው› አለው ‹ቅርጫት ስጠኝ ብየህ ነበር› ሲል መለሰለት፡፡ ተመልሶ ወደ በኣቱ ሲገባ ልቡናው በሰማያዊ ነገር ስለተመሰጠ ዘንግቶት ወደ ሽመናው ሥራ እንደገና ገባ፡፡ ለሦስተኛ ጊዜ ያ ወንድም ሲያንኳኳ አባ ዮሐንስ ተመልሶ ወጣና ‹ምን ፈልገህ ነው?› አለው፡፡ ‹ቅርጫት ስጠኝ ብየህ ነበር› አለና መለሰለት፡፡ አባ ዮሐንስም እጁን ይዞ እየጐተተ ወደ በኣቱ አስገባውና ‹ቅርጫት ከፈለግህ ያዝና ሂድ፣ በእውነቱ እንዲህ ላሉት ነገሮች እኔ ጊዜ የለኝም› አለው፡፡

5. አንድ ቀን አንድ ሰው ወደ አባ ዮሐንስ ሐፂር በኣት መጣና ሥራውን እያየ ያመሰግነው ጀምር፡፡ አባ ዮሐንስ ዝም  አለውና ገመድ መሥራቱን ቀጠለ፡፡ እንግዳውም እንደገና ወሬውን ቀጠለ፣ አባ ዮሐንስም ጸጥ አለው፡፡ ለሦስተኛ ጊዜ እንግዳው ወሬ ሲያበዛ፡፡ ‹አንተ ወደ በኣቴ በመግባትህ እግዚአብሔር ወጥቶ ሄደ› ብሎ ተናገረው፡፡

6. አባ ዮሐንስ እንዲህ አለ፡- ‹የብሕትውናን ኑሮ በከተማ ውስጥ የሚኖር አንድ ሽማግሌ ነበረ፡፡ ያ ሰው በከተማው ውስጥ ከፍተኛ ቦታ የሚሰጠውና ባለዝናም ነበር፡፡ አንድ አረጋዊ አባት ከማረፉ በፊት ያንን ሰው ሊያየው እንደሚፈልግ ለዚያ ሰው ጥሪ ደረሰው፡፡ ያም ሰው በቀን ከተጓዝኩ ሰዎች ስለሚከተሉኝ ለኔ የተለየ ክብር ይሰጡኛል ብሎ አሰበ፡፡ ስለዚህም በሌሊት ሰው ሳያየው ለመጓዝ ወሰነ፡፡ በመሸ ጊዜም አሁን ማንም አያየኝም ብሎ ተነሣና ጉዞ ጀመረ፡፡ ነገር ግን ሁለት መላእክት ታዝዘው መብራተ ይዘው መንገዱን ይመሩት ነበር፡፡ ይህንን የተመለከቱ የከተማው ሰዎች ወደ እርሱ ተሰባሰቡ፣ መላ ከተማው ያንን የመላእክት ብርሃን እያየ ከኋላ ተከተለው፡፡ ከክብር በሸሸ ቁጥር የበለጠ ክብርን አገኘ፡፡ በዚህም ‹ራሱን ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ይዋረዳል፣ ራሱንም የሚያዋርድ ሁሉ ከፍ ከፍ ይላል› የሚለው የወንጌል ቃል ተፈጸመ፡፡ (ሉቃ. 14.11)

7. አባ ጴሜን አባ ዮሐንስ እንዲህ ብሎ መናገሩን ገልጧል ‹ቅዱሳን በአንድ ቦታ የበቀሉ ዛፎችን ይመስላሉ፡፡ ከአንድ ምንጭ ጠጥተው፣ ልዩ ልዩ ዓይነት ፍሬ ያፈራሉ፡፡ የአንድ ቅዱስ ሥራ ከሌላው ይለያል፣ ነገር ግን በሁሉም አድሮ የሚሠራው አንድ መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡

ዋቢ   በበረሓው ጉያ ውስጥ


በረከተ ቅዱሳን ይደርብን

12 comments:

  1. I like it very much! it is very intresting ,God bless u.

    ReplyDelete
  2. Kale Hiwot Yasemalin!!

    ReplyDelete
  3. የአገልግሎት ጊዜህን ይባርክልህ ቃለ ህይወት ያሰማልን

    ReplyDelete
  4. KALE HIWOT YASEMALEN....EDMANA TANA YESTELN

    ReplyDelete
  5. ምን ያህል መታደል ነዉ?! ምናለ የነርሱን ትህትና ሩቡን ቢያድለን? ኢንጅነር ቃለህይወት ያሰማልን
    Sami zeGc

    ReplyDelete
  6. ሰርፀድንግልNovember 4, 2011 at 12:48 PM

    ቃለ ህይወት ያሰማልን!

    ReplyDelete
  7. ዲያቆን ቃለ ሕይወት ያሰማልን።
    በቸርነቱ አይለይህ።
    ፀጋውን ያብዛልህ።

    ReplyDelete
  8. kale hiwot yasemalen

    ReplyDelete
  9. Kale Yiwot Yasemalin! Dingil tabertah!

    ReplyDelete
  10. kale hiwot yasamalen
    keep doing

    ReplyDelete