Friday, September 23, 2011

ግሸን ደብረከርቤ ዳግማዊት ጎልጎታ - የግማደ መስቀሉ መገኛ


ግሸን ማርያም ደብር በወሎ ክፍለ ሀገር በአምባሰል አውራጃ ውስጥ የምትገኝ ደብር ናት፤ ይህች ደብር በሐይቅና በመቅደላ፤ በደላንታ፤ በየጁ መካከልና በበሸሎ ወንዝ አዋሳኝ በርዋ አንድ ዙሪያውን በገደል የተከከበች አምባ ናት፡፡ በበርዋ ከተገባ በኋላ ግቢዋ ከላይ ሜዳና መስቀለኛ ቦታ ነው፡፡ በትግራይ እንደ ደብረ ዳሞ በበጌምድር እንደዙር አምባ በመንዝ እንደ አፍቅራ ናት ፡፡

ወደዚህች ደብር ለመሔድ በረሐ አቋርጦ በሸሎን በመሻገር ፫ ሰዓት መንገድ አቀበት በመውጣት አንድ ቀን ሙሉ ተጉዞ ማታ ፲፪ ሰዓት ይገባል ፡፡ግሸን ማርያም በፊት ደብረ እግዚአብሔር ትባል ነበር ፡፡ይህ ደብረ እግዚአብሔር የሚለው ስያሜም በጻድቁ ንጉሥ ላሊበላ እጅ ከቋጥኝ ድንጋይ ተፈልፍሎ የተሠራ ቤተ መቅደስ በእግዚአብሔር  አብ ስም ስለነበረ ደብረ እግዚአብሔር ተብሎ የተጠራ ነው፡፡ ከዚያም በዓጼ ድግናዣን ዘመን መንግሥት የሐይቅ እስጢፋኖስ ገዳም ሲመሠረት ሐይቅ ደብር ነጎድጓድ ተብሎ ሲሰየም ግሸን  የሐይቅ ግዛት ስለሆነች ከደብረ እግዚአብሔር ደብረ ነጎድጓድ ተብላለች ፡፡

ከዚያም በ ፲፬ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ በዓጼ ዘርአ ያዕቆብ ዘመነ መንግሥት የክርስቶስ ግማደ መስቀሉ ግሸን ገብቶ ሲቀመጥ ከደብረ ነጎድጓድ ደብረ ከርቤ ተብላለች የደብሩ አስተዳዳሪም መምህረ እሥራኤል ዘደብረ ከርቤ ይባል ነበር፡፡ ከደብረ ከርቤ ግሸን ማርያም ተብላለች፡፡


የግማደ መስቀሉ መምጣት ታሪክ
ዓለምንና በውስጡ የሚገኘውን ሁሉ ፍጡር ፈጥሮ የሚገዛውን አምላክ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ቤተ እሥራኤል በቀራንዮ ላይ በመስቀል ሰቀሉት ፡፡ መድኃኔዓለም በዕለተ ዓርብ ከቀኔ በዘጠኝ ሰዓት ቅድስት ነፍሱን ከቅድስት ሥጋው በገዛ ሥልጣኑ ከለየ በኋላ በኋላ ከመስቀሉ አውርደው ቀበሩት ፡፡በ፫ኛው ቀን ሲነሣ ተሰቅሎ የነበረው የእንጨት መስቀል ሌት ተቀን በሙሉ ሳያቋርጥ እንደፀሐይ ሲያበራ በተጨማሪም አጋንንት ሲያባርር ድውይ ሲፈውስ ሙት ሲያነሣ ቤተ እሥራኤል አይሁድ ቀንተው በዓዋጅ ትልቅ ጉድጓድ ቆፍረው በመቅበር የቤት ጥራጊና አመድ ጠቅላላ የቆሻሻ መከማቻ እንዲሆን ወሰኑ፡፡ ከዚያ ዘመን ጀመሮ እስከ ሦስት መቶ ዘመን ድረስ የተከማቸው ቆሻሻ እንደተራራ ሆነ፡፡
ከዚያ በኋላ የታላቁ ቆስጠንጢኖስ እናት እሌኒ ንግሥት የተባለች ደግ ሴት የክርስቶስን መስቀል መስከረም ፲፯ ቀን ፫፻፳ ዓ.ም. ላይ በዕጣን ጢስ ምልክት ቁፋሮ አስጀምራ መጋቢት ፲ ቀን አግኝታ በማውጣት ታላቅ ቤተ መቅደስ ጎልጎታ ላይ ሠርታ በክብር አስቀመጠችው ይህ መስቀልም ከዚያ ዘመን ጀምሮ እንደ ፀሐይ እያበራ ድውይ እየፈወሰ አጋንንት እያባረረ ልዩ ልዩ ተአምራትን እየሠራ ሙት እያነሳ ዕውር እያበራ ተአምራቱን ቀጠለ፡፡ ይህንንም ከኃያላን ነገሥታት መካከል የፋርስ ንጉሥ መስቀሉን ማርኮ ፋርስ ወስዶ አስቀመጠው በዚህ ጊዜ የኢየሩሳሌም ምዕመናን የሮማውን ንጉሥ ሕርቃልን ዕርዳታ በመጠየቅ እንዲመለስ አድርገው በኢየሩሳሌም ብዙ ዘመን ሲኖር እንደገና ኃያላን ነገሥታት ይህን መስቀል እኔ እወስድ እኔ እወስድ እያሉ ጠብ ፈጠሩ፡፡
በዚህ ጊዜ የኢየሩሳሌም ፤ የቁስጥንጥንያ ፤ የአንጾኪያ ፤ የኤፌሶን ፤ የአርማንያ ፤ የግሪክ ፤ የእስክንድርያ የመሳሰሉት የሃይማኖት መሪዎች ጠቡን አበረዱት ከዚህም አያይዘው በኢየሩሳሌም የሚገኘውን የክርስቶስ መስቀል ከ፬ ከፍለው በዕጣ አድርገው በስምምነት ተካፍለው ከሌሎቹ ታሪካዊ ንዋያት ጋር በየሀገራቸው ወስደው በክብር አስቀመጡት፡፡ የቀኝ ክንፉ የደረሰው ለአፍሪቃ ስለነበር ከታሪካዊ ንዋያተ ቅድሳት ጋር በግብጽ የሚገኘው የእስክንድርያ ፓትርያርክ ተረክቦ ወስዶ በክብር አስቀመጠው፡፡
ይህ ግማደ መስቀልም ለብዙ ዘመን በእስክንድርያ ሲኖር በግብጽ ያሉ እስላሞች እየበዙ ኃይላቸው እየጠነከረ ሔደ በእስክንድርያ የሚኖሩትን ክርስቲያኖች ሥቃይ ያጸኑባቸው ጀመር ክርስቲያኖቹም አንድ ሆነው መክረው ለኢትዮጵያዊ ዓፄ ዳዊት እንዲህ የሚል መልዕክት ላኩ “ንጉሥ ሆይ! በዚህ በግብጽ ያሉ እስላሞች መከራ አጽንተውብናልና ኃይልህን አንሥተህ አስታግሥልን ብለው ጠየቁት” ዳግማዊ ዓፄ ዳዊትም ለመንፈሳዊ ኃይማኖት ቀንተው የክርስቶስ ፍቅር አስገድዶአቸው ፳ ሽህ ሠራዊት አስከትለው ወደ ግብፅ ዘመቱ በዚህ ጊዜ በግብፅ ያሉ ኃያላን ፈሩ ተሸበሩ ንጉሡ ዳግማዊ ዳዊትም እንዲህ የሚል መልዕክት ለእስላሞች ላኩ በተፈጥሮ ወንድሞቻችሁ ከሆኑት ክርስቲያኖች ጋር ካልታረቃችሁ ሀገራችሁን መጥቼ አጠፋዋለሁ የሚል ማስጠንቀቂያ ላኩ ፡፡የንጉሡ መልዕክት ለእስላሞች እንደደረሳቸው ፈርተው እንደጥንቱ በየሃይማኖታቸው ፀንተው በሰላም እንዲኖሩ ከክርስቲያን ወንድሞቻቸው ጋር ታረቁ፡፡
 መታረቃቸውን ዳግማዊ ዳዊት ሰሙ በዚህም ጉዳይ ንጉሡ በጣም ደስ አላቸው እገዚአብሔርንም አመሰገኑ በግብፅ የሚኖሩ ክርስቲያኖችም ከ፲፪ ሺህ ወቄት ወርቅ ጋር ደስታቸውን ለኢትዮጵያዊው ንጉሥ  ለዳግማዊ ዳዊት በደብዳቤ አድርገው ላኩላቸው ንጉሡም የደስታውን ደብዳቤ ተመልከተው ደስ ኣላቸው ፤ ወርቁን ግን መልሰው በመላክ እንዲህ የሚል ደብዳቤ ፃፉ በግብፅ የምትኖሩ የክርስቶስ ተከታዮች ሆይ እንኳን ደስ አላችሁ የላካችሁልኝን ፲፪ ሺህ ወቄት ወርቅ መልሼ ልኬላችኋለሁ የእኔ ዓላማ ወርቅ ፍለጋ አይደለም የክርስቶስ ፍቅር አስገድዶኝ በተቻለኝ ችግራችሁን ሁሉ አስወገድኩላችሁ አሁንም የምለምናችሁ በሀገሬ በኢትዮጵያ ረሀብና ቸነፈር ድርቅ ስለወረደብኝ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተሰቅሎበት የነበረውን መስቀልና የቅዱሳንን አፅም ከሌሎች ክቡራን ዕቃዎች ጋር እንድትልኩልኝ ነው የሚል ነበር፡፡
በእስክንድርያም ያሉ ምእመናን ይህ መልዕክት እንደደረሳቸው ከሊቃነ ጳጳሳቱና ከኤጲስ ቆጶሳቱ ጋር ውይይት በማድረግ ይህ ንጉሥ ታላቅ ክርስቲያን ነው፡፡ ስለዚህ ልቡን ደስ እንዲለው የፈለገውን የጌታችንን ግማደ መስቀል ከቅዱሳን አጽምና ንዋየ ቅድሳት ጋር አሁን በመለሰው ፲፪ ወቄት ወርቅ የብርና የንሐስ የመዳብና የወርቅ ሣጥን አዘጋጅተን እንላክለት ብለው ተስማምተው በክብር በሥነ ሥርዓት በሠረገላና በግመል አስጭነው ስናር ድረስ አምጥተው ባስረከቡአቸው ጊዜ በእጃቸው እያጨበጨቡ በእግራቸው እያሸበሸቡ በግንባራቸው እየሰገዱ በክብር በደስታ ተቀበሉት ይህም የሆነው መስከረም ፳፩ ቀን ነው፡፡ በኢትዮጵያም ታለቅ ብርሃን ሌት ተቀን ፫ ቀን ሙሉ ሲበራ ሰነበተ፡፡
ግማደ መስቀሉ ወደ መካከለኛው ኢትዮጵያ ሳይደርስ በድንገት ዓፄ ዳዊት ስናር ላይ አረፉ፡፡ ግማደ መስቀሉም የግድ በዚያው በስናር መቆየት አስፈለገው፡፡ ከዚህ በኋላ የሟቹ የዳግማዊ ዳዊት ልጅ ዘርአ ያዕቆብ እንደነገሡ ወደ ሥናር ሔደው ግማደ መስቀሉን ከሌሎቹ ንዋያተ ቅድሳት ጋር አምጥተው በመናገሻ ከተማቸው በደብረ ብርሃን ላይ ቤተ መቅደስ ሠርተው ለማስቀመጥ ሲደክሙ በሕልማቸው አንብር መስቀልየ በዲበ መስቀል ወዳጄ ዘርአ ያዕቆብ ሆይ መስቀሌን በመስቀልኛ ቦታ ላይ አስቀምጥ የሚል ሕልም አዩ ፡፡ ንጉሡም መስቀለኛ ቦታ እየፈለጉ በኢትዮጵያ አውራጃዎች ሁሉ መስቀለኛ ቦታ በመፈለግ ከብዙ ቦታ ላይ አስቀምጠውት ነበር ለምሳሌ በሸዋ በደርሄ ማርያም ፤ በመናገሻ ማርያም ፤ በወጨጫ መስቀሉን አሳርፈውት ነበር፡፡ ነገር ግን የመጨረሻውን ቦታ ያላገኙ በመሆኑ በራዕይ እየደጋገገመ መስቀሌን በመስቀልኛ ቦታ ላይ አስቀምጥ እያለ ይነግራቸው ነበር፡፡
ዓፄ ዘርአያዕቆብም ለ፯ ቀናት ያህል ሱባዔ ገቡ በዚያም የተገለፀላቸው መስቀልኛውን ቦታ የሚመራህ ዓምድ ብርሃን ይመጣል አላቸው እርሳቸው ከዚያ እንደወጡ መስቀለኛውን ቦታ የሚመራ ዓምደ ብርሃን ከፊታቸው መጥቶ ቆመ በዚያ መሪነት ወደ ወሎ ክፍለ ሀገር አምባሰል አውራጃ ውስጥ ግሸን ከምትባል መርቶ አደረሳቸው ፡፡በርግጥም ይህች ግሽን የተባለች አምባ ጥበበኛ ሰው እንደቀረፃት የተዋበች መስቀልኛ ቦታ ሁና ስለአገኟት የልባቸው ስለደረሰ ደስ አላቸው ፡፡ በዚያችም አምባ ታላቅ ቤተ መቅደስ ሠርተው መስቀሉንና ሌሎች ንዋያተ ቅድሳቱን በየማዕረጋቸው የክብር ቦታ መድበው አስቀመጧቸው ዘመኑም በ፲፬ ኛው ክፍለ ዘመን ነው፡፡
v ከእስክንድርያ ሀገር ከመስቀሉ ጋር በልዩ ልዩ ሣጥን ተቆልፈው የመጡትም ዝርዝር
v ጌታ በዕለተ ዓርብ ለብሶት የነበረው ቀይ ልብስ ከሮም የመጣ ከለሜዳው
v ከአፍርጌ ሀገር የመጣው ሐሞት የጠጣበት ሰፍነጉ
v ዮሐንስ የሳለው የኲርዓተ ርዕሱ ስዕል
v ቅዱስ ሉቃስ የሣላቸው የእመቤታችን ስዕሎች
v የበርካታ ቅዱሳን አጽምና በኢየሩሳሌም ውስጥ ከልዩ ልዩ ቅዱሳት መካናት የተቆነጠረ የመሬት አፈር
v የዮርዳኖስ ውሃ
በግብጽ ውስጥ ከሚገኙት ታላላቅ ገዳማት የተቆነጠረ አፈር ነው፡፡ የነዚህንም ዝርዝር ለኢትዮጵያ ሕዝብና ለግሼን ካህናት መስከረም ፳፩ ቀን ፩ ሺ ፬፻፵ ዓ.ም. ላይ ተናገሩ ፡፡በመጀመሪያም ይህ ግማደ መስቀል ከእስክንድርያ ስናር የገባው መስከረም ፲ ቀን ነው ወደ ኢትዮጵያም የገባው በመስከረም ፳፩ ቀን ነው፡፡ አሁንም በመጨረሻ ግሸን አምባ የገባው መስከረም ፳፩ ቀን ሲሆን ቤተ መቅደስ ተሠርቶ ቅዳሴ ቤቱ የተከበረውና አፄ ዘርዓያዕቆብ ለመላው ኢትዮጵያ በፅሑፍ በመዘርዘር የገለፁበትም መስከረም ፳፩ ቀን ነው፡፡
ስለዚህ ከዚህች በግሸን ደብር የክርስትና እምነት ያላቸው የኢትዮጵያ ምእመናን ከበረከተ መስቀሉና ከቅዱሳን አፅም በረከት ለማገኘት በየዓመቱ መስከረም ፳፩ ቀን እየመጡ ያከብራሉ፡፡ በዚያም ዘመን የነበሩት የኢትዮጵያ ጳጳሳት የነበሩት አባ ሚካኤልና አባ ገብርኤል የተባሉ ከንጉሡ ከዓፄ ዘርአ ያዕቆብ ጋር ሆነው የምህረት ቃል ኪዳን ለመቀበል በዚህች በግሸን ደብር ሱባዔ ገቡ በሱባዔአቸውም በመጨረሻ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተገልጾ ይህች ቦታ እኔ ተወልጄ ያደኩባትን ኢየሩሳሌምን ትሁን የተሰቀልኩባትን ቀራንዮን ትሁን የተቀበርኩባትንም ጎልጎታን ትሁን በዚች ቦታ እየመጣ የሚማፀነውን ሁሉ ቸርነቴ ትጎበኘዋለች ጠለ ምህረቴንም አለይባትም ፤  ከሩቅም ሆነ ከቅርብ መጥቶ የተቀበረ ኢየሩሳሌም እንደተቀበረ ይሁን የሚል የምህረት ቃል ኪዳን ተገልጾላቸው በዚህ ለተገኙት ምዕመናን ሁሉ በጽሑፍ ካሰሙ በኋላ ጠቅላላ የግማደ መስቀሉንና የሌሎቹን ታሪካውያን ንዋያተ ቅዱሳትንም ዝርዝር ታሪክ የያዘውን መጽሐፈ ጤፉት ብለው ሰይመው ድንጋጌውን ሁሉ በመዘርዘር ለግሸን እግዚአብሔር አብ ሰጡ፡፡
 አፄ አርዓ ያዕቆብም በዚህ ብቻ ሳይወሰኑ እሌኒ እኅታቸው  የተሰኘችው በእመቤታችን ማርያም ስም ቤተ መቅደስ እንድትሠራ አዘው የእመቤታችን ማርያም ቤተ ክርስቲያን ከእግዚአብሔር አብ ቤተ ክርስቲያን አጠገብ  አሳንጻ ጥር ፳፩ ቀን ቅዳሴ ቤቱ ተከበረ ዓፄ ዘርአ ያዕቆብም ይህችን ደብር ደብረ ከርቤ ብለው በመሰየም እንኳንስ ሰው የሠገረ ቆቅ ፤ የበረረ ወፍ እንዳይገደል ዳሯ እሳት መሀሏ ገነት ትሁን ብለው ደንብና ሥርዓት በጤፉት መጽሐፍ ውስጥ አጽፈዋል፡፡ በዚህ ምክንያት በየጊዜው የነገሡ የኢትዮጵያ ነገሥታትና የተሾሙ ጳጳሳት መሳፍንትና መኳንንት ልዩ ልዩ ንዋያተ ቅድሳትንና መጻሕፍትን የወርቅንና የብርን ሰን ፤ ብርና ጻሕል ጽዋን መስቀልን የመሳሰሉትን የሰጧት ምዕመናንም በየዓመቱ መስከረም ፳፩ ቀን በግሸን ማርያም ለመገኘት ከዓመት ወደ ዓመት እየበረከቱ ሔደዋል፡፡
በመስከረም 10 ፤ መስከረም 17 በዓለ መስቀል እና መስከረም 21 የግሸን በዓል ታሪክ ከረጅም በአጭሩ ይህንን ይመስላል ፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያ ምዕመናን የሆናችሁ ሁሉ ከበረከተ መስቀሉ ለመሳተፍ ወደ ግሸን ገሥግሱ፡፡


ልዑል እግዚአብሔር ከበረከተ መስቀሉ ያሳትፈን 
አሜን
መልካም የመስቀል በዓልስምዓት
v ትንሣኤ መጽሔት
v መለከት መጽሔት

12 comments:

 1. Thanks Deacon Melaku, Amen for that.
  Dawit was a great person for Ethiopian Orthodox church and the country as a whole. He brought a lot of things from Egypt for our country's sake.

  We want the current leaders to take some lesson from him and bring Nile back to Ethiopia. Dawit could manage to bring Egyptian owned property, while our generation leaders can't even secure our own water.

  God has purpose for everything that is happening in this world. God bless Ethiopia!

  Abebaw

  ReplyDelete
 2. kale hiwot Yasemalen!

  ReplyDelete
 3. ቃለ ህይወት ያሰማልን በእድሜ በጤና ይጠብቅልን
  ሌላ መስጠት ምፈልገው አስተያየት ቢኖር የምትፅፋቸው ነገሮች ሁሉ በጣም ጥሩ ናቸው ነገር ግንሰዎች ኮምፒዩተሮቻቸው ላይ አማርኛ ፎንት ከሌለ ማንበብ አይችሉን ስለዚህ ፖስት በምታደርግበት ጊዜ ወደ pdf ተቀይሮም ቢቀመጥ ጥሩ ነው የሚል አስተያየት አለኝ
  እናመሰግናለን

  ReplyDelete
 4. ቃለ ሕይወት ያሰማልን ዲን መልአኩ
  በአካል መሄድ ላልቻልን ግሸንን በዓይነ ሕሊና እንድናያት አደረግከን በእምነትም ከቅድስ+ቱ መካን ቃልኪዳን ተሳተፍን ጌታችን ያለበሱት ቀይ ከሌሜዳ ቅዱሰ ሉቃስ የሳላት የቅድስት ንጽሕት ልዕልት ክብርትም የሆነች የእናታእን ስዕለ አድኅኖም ተመለከትን
  በኪደተ እግር እንጎበ’ት ዘንድ አምላክ በቸርነቱ ይርዳን

  ReplyDelete
 5. ቃለ ሕይወት ያሰማልን

  ReplyDelete
 6. kale hiwoten yasemalen tsegawen yabezaleh

  ReplyDelete
 7. ዲያቆን ቃለ ሕይወት ያሰማልን።
  ጸጋውን ያብዛልህ።

  ወስብሐት ለእግዚአብሔር።

  ReplyDelete
 8. kale hiwote yasamalen

  ReplyDelete
 9. ፍሊጶስ እምቤተ አስድሮሥSeptember 30, 2011 at 9:54 AM

  ዉድ ወንድማቺን ዲ /ን መላኩ አግዚአብሔር አምላክ ፅናቱን እና ብርታቱን ያድልህ።መልካም የመስቀል በዓል ይሁንልህ

  ReplyDelete
 10. ቃለ ህይወት ያሰማልን የመስቀሉ ፍቅር በሁላችን ላይ ይደር የበረከቱ ተካፋይ ያድርገን! ክርስቲያን ሁሉ ሊጐበኝው የሚገባ! ልዩ መንፈሳዊ ፍቅር ያላት ቦታ መንፈሳዊ እርካታ የምትሰጥ ነች ጊሸን ደብረከርቤ፤

  ReplyDelete