Wednesday, June 22, 2011

ቅዱሳን ሐዋርያት ክፍል ፩

መግቢያ
መድኃኒተ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ በ30 ዘመኑ በማየ ዮርዳኖስ በዕደ ዮሐንስ ተጠምቆ 40 ቀንና ሌሊት በገዳመ ቆሮንቶስ ከጾመ ከጸለየ በኋላ የማስተማር ሥራውን ሲጀምር አስቀድሞ ያደረገው ነገር ቢኖር ቃሉን ተምረው ሰምተው ተአምራቱን አይተው ዳስሰው በዓለም ዞረው ወንጌልን የሚሰብኩ ደቀ መዛሙርቱን መምረጥ ነበር፡፡ እነዚህ ደቀ መዛሙርቱም ሐዋርያት ተብለው ይጠራሉ፡፡



ሐዋርያ የሚለው ቃል ሖረ-ሄደ ካለው የግእዝ ቃል የወጣ ሲሆን ትርጉሙም የተላከ ሂያጅ፣ ልዑክ ማለት ነው፡፡ ወንጌለ መንግሥትን ድኅነተ ዓለምን ለመላው ዓለም ሊያውጁ ሊያበሥሩ ተልከዋልና፡፡ ቅዱስ ማርቆስ በወንጌሉ እንደገለጠው (ማር. 3.13) አስቀድሞ ከእርሱ ጋር እንዲኖሩ ከጠራቸው በኋላ እግዚአብሔር ለሰው ልጅ የገለጠውን ድንቅ ሥራ አምላክ ሰው ሆኖ ያደረገውን ተአምራት ለዓለም ድኅነት የተደረገውን ሁሉ ሊመሠክሩ ተመርጠዋል፡፡
ከዚያ በፊት በሌዋውያን ዘር ይወርድ የነበረውን የብሉይ ኪዳን ሥልጣነ ክህነት በሐዲስ በመተካት ለእነርሱ ሰጣቸው ዮሐ. 20.22፡፡ እነርሱም ጌታችን እንዳስተማራቸውና ቃል ኪዳንም እንደገባላቸው፡፡ ማቴ. 28.20፡፡ ለተከታዮቻቸው ይኸንን ሥልጣን በአንብሮተ ዕድና በንፍሐት በመሾም አስተላለፉ፡፡ የሐዋ. 9.12፡፡በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ደም የተዋጀችውን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን በስብከታቸው በሰጣቸውም ሥልጣን ባደላቸውም ጸጋ ጠብቀው አቆዩዋት፡፡

የመጀመሪያዋ ቤተ ክርስቲያን በበዓለ ሃምሳ በቅዱስ ጴጥሮስ ስብከት በ3000 ምእመናን በሀገረ ኢየሩሳሌም በ0034 ዓ.ም ተመሠረተች፡፡ ከዚያም ዓለምን ዕጣ በዕጣ ተካፍለው ተዘዋውረው አስተማሩ፡፡ ወንጌልን ሰብከው ቤተ ክርስቲያንን አነፁ፡፡ አምልኮ ጣዖትን አጠፉ፡፡ ርኩሳን አጋንንትን አሳደዱ፡፡ በመስቀል ዕርፍ አርሰው ንጹሕ ዘር ወንጌልን ዘርተው በደማቸው አተሙ፡፡

ላስተማሩት  ሕዝብ ለእምነቱ ማጽኛ የሚሆኑ መልእክታትን ጻፉ፡፡ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን ሠሩ፡፡ ከጌታ የተማሩትን ያዩትን እና የሰሙትን ለተከታዮቻቸው በቃልም በኑሮም በመጻሕፍትም አውርሰው በተጋድሎ ዐረፉ፡፡

የሐዋርያት አመራረጥ
ጌታችን ሐዋርያትን ከድኾችም ከሀብታሞችም መርጦአል፡፡ እነ ቅዱስ ጴጥሮስን የመሰሉ ድኻ ዓሣ አጥማጆችን ሲጠራ እነቅዱስ ማቴዎስን የመሰሉ በቀረጥ ብር የከበሩትንም አልተዋቸውም፡፡ ሁሉም በእግዚአብሔር ዘንድ እኩል ናቸውና፡፡ ሁሉም ደግሞ ያላቸውን ትተው ተከታትለውታል፡፡ ማቴ. 4.20፤ 9.9፡፡
         ከተማሩትም ከማይማኑም ወገን መርጦአል፡፡ ዮሐንስና ያዕቆብን ጌታ የጠራቸው ከአባታቸው ጋር ዓሣ ሲያጠምዱ ነው፡፡ ሌላ ትምህርት አልነበራቸውም፡፡ ነገር ግን አልናቃቸውም፡፡ ምሁረ ኦሪት የነበረውንም ናትናኤልን ጠርቶታል አልተወውም፡፡
የቀናተኞች አይሁድ ወገን በመሆኑ በዚያን ዘመን ሮማውያንን ለማስወጣት ውስጥ ውስጡን በምድረ ፍልስጥኤም ይካሄድ የነበረው ዐመፅ ተካፋይ የነበረውን ስምዖንን ከዚያ ግርግር አውጥቶ የሰላምና የፀጥታ ወደብ ወደ ሆነው ወደ እርሱ ወስዶታል፡፡
   ቤተ እሥራኤል ስትመሠረት 12ቱ አበው እየተባሉ በሚጠሩት ከያዕቆብ አብራክ በተከፈሉ የአሥራ ሁለቱ ነገድ አባቶች ነበር፡፡ አሁንም የእሥራኤል ዘነፍስ ማኅበር ቤተ ክርስቲያን ስትመሠረት በ12ቱ ሐዋርያት ትሆን ዘንድ አምላክ ፈቀደ፡፡
  1. ቅዱስ ጴጥሮስ - ከቤተ ስምዖን (በእናቱ ወገን) እናቱ ትወደው ስለነበር በነገድዋ ስም ጠራችው፡፡
  2. ቅዱስ እንድርያስ - ከቤተ ሮቤል (በአባቱ ወገን) አባቱ ይወደው ነበርና ከነገዱ በተወረሰ ስም ጠራችው፡፡
  3. ቅዱስ ያዕቆብ - ከነገደ ሌዊ (በአባቱ)
  4. ቅዱስ ዮሐንስ -  ከነገደ ይሁዳ (በእናቱ)
  5. ቅዱስ ፊልጶስ -  ከነገደ ዛብሎን
  6. ቅዱስ በርተሎሜዎስ - ከነገደ ንፍታሌም
  7. ቅዱስ ማቴዎስ - ከነገደ ይሳኰር
  8. ቅዱስ ቶማስ - ከነገደ አሴር
  9. ቅዱስ ያዕቆብ ወልደ እልፍዮስ - ከነገደ ጋድ
  10. ቅዱስ ታዴዎስ -  ከነገደ ዮሴፍ
  11. ቅዱስ ስምዖን ቀነናዊ - ከቤተ ብንያም
  12. ያስቆሮቱ ይሁዳ - ከቤተ ዳን


የሐዋርያት ሲኖዶስ
ሲኖዶስ ቃሉ የግሪክ ሲሆን ትርጉሙም ስለ ነገራተ ቤተ ክርስቲያን የሚሰበሰቡ  የቤተ ክርስቲያን አባቶች  ጉባዔ ማለት ነው፡፡

የመጀመሪያዋ የሐዋርያት ሲኖዶስ የተደረገችው በ50 ዓ.ም አካባቢ በኢየሩሳሌም ከተማ ሲሆን ለጉባዔው መደረግ ምክንያት የሆነውም በአንጾኪያ ቤተ ክርስቲያን ከይሁዲነት በተመለሱትና ከአረማዊነት በተመለሱት መካከል የተነሣውን ክርክር ለመፍታት ነበር፡፡

ቅዱሳን ሐዋርያት በተሰበሰቡ ጊዜ ሁሉ ስለ ነገረ ቤተ ክርስቲያን፣ ስለ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን፣ ስለ ካህናት አገልግለት ስለ ምእመናን ድርሻ፣ ስለ ቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ውሣኔዎችን አስቀምጠዋል፡፡ እነዚህ ‹እነርሱና መንፈስ ቅዱስ› በአንድ ላይ ሆነው የወሰኑዋቸው ውሣኔያት በሲኖዶስ፣ በአብጥሊስ፣ በግፅው፣ በዲደስቅልያ ወዘተ. መጻሕፍቶቻቸውና በቤተ ክርስቲያን ትውፊት ለኛ ደርሰውናል፡፡

ዛሬም በቅድስት ቤተ ክርስቲያን በዓመት ሁለት ጊዜ የሊቃነ ጳጳሳት ጉባዔ (ሲኖዶስ) የሚደረገው በዚሁ መሠረት ነው፡፡

አዕማድ ሐዋርያት
ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ለገላትያ ክርስቲያኖት በላከው መልእክቱ (2፡9) ጴጥሮስ፣ ዮሐንስ እና ያዕቆብን ‹አዕማድ ሐዋርያት› በማለት ጠርቷቸዋል፡፡ ይህ ስም ሊሰጣቸው የቻለበት ዐቢይ ምክንያት የኢየሩሳሌምን ቤተ ክርስቲያን በዋናነት ያስተባበሩ ስለነበር ነው፡፡
ከዚህም በተጨማሪ እነዚህ ሦስቱ ሐዋርያት ‹የምሥጢር ሐዋርያት› እየተባሉም ይጠራሉ፡፡ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ
·        በደብረ ታቦር ምሥጢረ መለኮቱን ሲገልጥ
·        በኢያኢሮስ ቤት ልጁን ሲፈውስ
·        በጌቴሴማኒ ሲጸልይ ከሌሎች ለይቶ ይዟቸው ሄዶ ነበር፡፡

ለሐዋርያት የተሰጠ ፀጋ
ጌታችን በቂሣርያ ከተማ ለሐዋርያት ያቀረበውን ጥያቄ በመመለሱ ቅዱስ ጴጥሮስን ‹የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ በሰማያት ያለው አባቴ እንጂ ሥጋ እና ደም ይህን አልገለጠልህም፡፡ አንተ ብፁዕ ነህ፡፡ እኔም እልኻለሁ አንተ ጴጥሮስ (ዐለት-በላቲን) ነህ፡፡ በዚህች ዐለትም ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራለሁ፡፡ የገሃነም ደጆችም አይችሉአትም፡፡ የመንግሥተ ሰማያትን መክፈቻዎች እሰጥኻለሁ፡፡ በምድር የምታሥረው በሰማያት የታሠረ ይሆናል፡፡ በምድር የምትፈታው በሰማያት የተፈታ ይሆናል፡፡› ማቴ. 16.17-19 የሚለውን ቃል ተናግሮታል፡፡
ቅዱስ ጴጥሮስ ይህንን ለመባል የበቃው የክርስትና እምነት መሠረት የሆነውን ምሥጢረ ሥጋዌን - ምሥጢረተዋሕዶን በመመስከሩ ነው፡፡ አይሁድ የዮሴፍ ልጅ ነው፤ ሌሎቹ ደግሞ ከነቢያት አንዱ ነው፡፡ ሲሉ የክርስቶስን የባሕርይ አምላክነት ቁልጭ አድርጎ በመመስከሩ ምስክርነቱም የእምነት መሠረት ነውና ‹ዐለት› ተባለ፡፡ የክርስትና እምነት መነሻው የእግዚአብሔር አብ የባሕርይ ልጅ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ሊያድነን ሊዋጀንም መጣ ብሎ ማመን ነው፡፡
ጌታችን ቅዱስ ጴጥሮስ ‹ዐለትነህ› ያለው ስለ እምነቱ ነው፡፡ ሰዎችን ታናሽ ወይም ታላቅ፣ ብፁዕ ወይንም ሌላ የሚያደርጋቸው እምነታቸው ነውና ለዚህ ነው ጌታችን በመዋዕለ ትምህርቱ ብዙ ጊዜ ‹እምነትህ(ሽ) ታላቅ ነው› ይል የነበረው፡፡
‹የመንግሥተ ሰማያት ቁልፍ› ለሐዋርያት የተሰጠውን ሥልጣነ ክህነት የሚያሳይ ነው፡፡
በምድር ያሠሩት፡- ከምእመናን ልቡና እያወጡ ያሠሩት ጠላት ዲያብሎስ፣ ርትዕት የሆነችውን ሃይማኖት ሊያጣምም ሲሞክር በስንዴው አዝመራ እንክርዳድን ሲዘራ ተገኝቶ አውግዘው የለዩት መናፍቅ በሰማያትም የታሠረ፣ የተለየ፣ የተወገዘ ይሆናል፡፡ እንኳንስ በሐዲስ ኪዳን ጥንት በሕገ ልቡና ዘመን አብርሃም የባረከውን ይስሐቅ፣ ይስሐቅ የባረከውን ያዕቆብ እግዚአብሔርም በሰማያት በረከት ሲባርካቸው የለዩዋቸውን እስማኤልንና ዔሳውን ደግሞ ከበረከቱ ለይቷቸዋል፡፡
በምድር፡- የፈታኸው፡- ዓለም በበደል በኃጢአት የታሠረ ነውና የኃጢአትን ገመድ በወንጌል ሰይፋቸው በጣጥሰው በፊት ቢፈቱለት በንስሐ በቀኖና ቤተ ክርስቲያን ከበደል እሥራት ቢፈቱት በሰማያት ፍርድ፣ በሰማያት መዝገብ የተፈታ ነፃም የወጣ ይሆናል፡፡
ይህ ሥልጣነ ክህነት ለቅዱስ ጴጥሮስ ብቻ የተሰጠ ሳይሆን ሐዋርያትን ሁሉ ወክሎ የተቀበለው ነው፡፡ ይህ ባይሆን ኖሮ በወንጌል ብርሃን የኃጢአትን ጨለማ እንዲገልጡ፣ የታሠሩትን እንዲፈቱ ጌታችን ሐዋርያትን ሁሉ ወደ ዓለም ባልላከም ነበር፡፡ መላክ የሚገባው ቅዱስ ጴጥሮስ ብቻ ነበርና፡፡
ይህንንም ሲያረጋግጥልን ጌታችን ለሐዋርያት የመንፈስ ቅዱስን ሀብት ባደለበት ሥልጣነ ክህነትን (አስቀድሞ የነገራቸውን፤  ያበሠራቸውን፣ ቃል ኪዳንም የገበላቸውን) ሲሰጣቸው ‹እፍ አለባቸውና መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ፡፡ ኃጢአታቸውንም ይቅር ያላችኋቸው ሁሉ ይቀርላቸዋል፡፡ የያዛችሁባቸውም ተይዞባቸዋል፡፡› በማለት ቀድሞ በቁልፍ የተመሠለ ሥልጣናቸውን አብራርቶ ተረጉሞ ነግሮዋቸዋል፡፡ ዮሐ. 20.22-23፡፡
ይህም ሥልጣን በአንብሮተ ዕድ ለቤተ ክርስቲያን ካህናት ተላልፎአል ይተላለፋልም፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንኳን ከተጠመቀ በኋላ ይህንን ሀብት በአንብሮተ ዕድ አግኝቶታል፡፡ የሐዋ. 9.12፡፡ እርሱም በፈንታው እነ ቅዱስ ጢሞቴዎስንና ቲቶን በዚሁ ሥልጣን ሾሟቸዋል፡፡ የመንፈስ ቅዱስ ልጁን ጢሞቴዎስንም ‹በማንም ላይ ፈጥነህ እጅህን አትጫን› በማለት ያዘዘው ይህንን ሥልጣነ ክህነት ለእግዚአብሔር ቤት አገልግሎት ለተመረጡ፣ ራሳቸውንም ወደው ፈቅደው ለለዩ፣ ለምእመናን አባት፣ መሪ መሆን ለሚችሉ ብቻ መስጠት ስላለበት ነው፡፡
ከሁሉም በላይ ደግሞ መድኃኒተ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ በሚያርግበት ሰዓት ‹እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ከእናንተ ጋር ነኝ› ማቴ. 28.20 በማለት የተናገረው ሐዋርያት ሳይሞቱ በዚህች ምድር የሚኖሩ ሆነው ሳይሆን በእነርሱ እግር ተተክተው ቤተ ክርስቲያንን ለሚያገለግሉ ካህናት ጭምር ይህንን የሐዋርያት ሥልጣን ማደሉን ሲናገር ነው፡፡ 
የሐዋርያት ትምህርት - ለቤተ ክርስቲያን
ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የተሰበከችው በሐዋርያት በመሆኑ ትምህርተ ሐዋርያት ከክርስቶስ የተገኘ የቤተ ክርስቲያን እምነት መነሻ ነው፡፡ የሐዋርያት ትምህርት በዓይን ያዩት፣ በጆሮ የሰሙት፣ በእጅ የዳሰሱት በኋላም በመንፈስ ቅዱስ የተረዱት ነውና እውነተኛነቱ የተረጋገጠ ነው፡፡
በመድኃኒተ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ‹ሂዱና አስተምሩ› ተብለው የታዘዙ ናቸውና መልእክተኛነታቸው የታመነ ነው፡፡ የእነዚህን ሐዋርያት ትምህርት ቤተ ክርስቲያን 1.ኛ በትውፊት 2.ኛ በመጻሕፍት አግኝታዋለች፡፡
1. ትውፊት
ሐዋርያት ቅዱስ ጳውሎስ በመልእክቱ ‹ከእኔ የተማራችሁትንና የተቀበላችሁትን፣ የሰማችሁትንም ያያችሁንትም እነዚህን አድርጉ› ፊልጵ 4.9 ፡፡ በማለት እንደተናገረው ሐዋርያት ያስተማሩት በመጻሕፍት ብቻ ሳይሆን ከኑሮአቸው፣ ከተግባራቸው፣ ከገድላቸው እና ከትሩፋታቸው ጭምር በመሆኑ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በሐዋርየት  ትውፊት ትጠቀምበታለች፡፡
2. በሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት
የሐዋርያትን እውነተኛ ትምህርት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ጠብቃ በመያዝ ለዓለም  አበርክታዋለች፡፡ ሐዋርያት ወንጌልንና መልእክታትን የጻፉት ያስረከቡትም ለቤተ ክርስቲያን ነው፡፡ የሚገኘውም በቤተ ክርስቲያን ነው፡፡ የመጽሐፍ ቅዱስ ባለቤትም ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡
ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን የትምህርቷ፣ የሥርዓቷና የሕጓ መሠረት መጽሐፍ ቅዱስ የሆነውም በዚሁ መሠረት ነው፡፡ 
                                                                      ይቆየን
ዋቢ ፡ ቤተክርስቲያንህን ዕወቅ መጽሐፍ

         ዜና ሐዋርያት
        

10 comments:

  1. +++

    ለመጀመር እንደተነቃቃህ በርታ ብለህ በተለይ ዓይን ስንክሳሩን እንደምታስኮሞኩመን ተስፋ አደርጋለሁ።

    መክ.

    ReplyDelete
  2. selame dn mele endemen alehe betame teru gemere new ena berta eshe

    ReplyDelete
  3. Kale Hiwot Yasemalin Diakon Melaku, I have a comment on the picture you post above. Is this picture represent our church. There was no this kind of supper on that night. Yihin hibist Yihin Tsiwa Ale enji Hulum Yerasachewin yizew Ayilim ena lewedefitu Tinikake Bideregibet Lamalet. Yejimare ena Yefitsame Balebet Ersu Yirdah>

    ReplyDelete
  4. በእድሜ ቤጤና ይጠብቅልን::

    ReplyDelete
  5. yeagelgelot zemenehen yarzemelen

    ReplyDelete
  6. The wording and the information contained in the writing is in line with the teaching of Our Church. And it is very useful

    ReplyDelete
  7. it is good job. But I have something to say with regard to the picture you used - the last supper, I donot think it it the right picture.

    ReplyDelete
  8. ejig grum new, egzer tsegawun yabzalih

    ReplyDelete
  9. አንተነህ: ስለስዕል ጥቆማሕ ልክ ነው ፧ ሐሳብክን እጋራለሑ።
    ለወንድማችን ቃለ ሔይወት ያሰማልን ።

    ReplyDelete